“ልክ እናስገባቸዋለን” ጊዜ ያለፈበት የፉከራ ቃል
Kiyyaa Gonfaa
ከሰሞኑ አቶ አባይ ፀሃዬ አዲሱን የፊንፊኔ ማስተር ፕላን አስመልክተው የተናገሩት የዛቻና የፉከራ ቃል መላውን የኦሮሞ ህዝብ ያስቆጣና ምናልባትም አዲሱ የማስተር ፕላን ፕሮግራም በኦሮሞ ህዝብ ዘንድ ፍፁም ተቀባይነት የሌለው እና ከባድ መስዋትነት የተከፈለበት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የአቶ አባይ ፀሃዬ “ልክ ይገባሉ” የሚለው ያረጀና ጊዜው ያለፈበት የፉከራ ቃል የኦሮሞን ህዝብ በበለጠ ለነፃነቱ የሚያደርገውን ትግል አጠናክሮ እንዲቀጥል የሚያነሳሳ ንቀት የተሞላበት ንግግር ነው::
እንዲህ ያለው ዛቻና ማስፈራሪያ ለዘመናት የተጨቆነንና የነፃነት ጥያቄን አንግቦ የተነሳን ሰፊ ህዝብ በይበልጥ እንዲጠናከርና የተፈረደበትን የልክ ይገባል ዛቻ አፀፋዊ ምላሽ ለመስጠት እራሱን ዝግጁ እንዲያደርግ የሚጋብዝ ባለንበት ዘመን ሊሰነዘር የማይገባ አፀያፊ ቃል ነው:: ተናጋሪው የወቅቱ ባለስልጣን በተለይ በኦሮሚያ ክልላዊ መስተዳድር በየደረጃው የሚገኙ ባለስልጣናትን ለአዲሱ የፊንፊኔ ማስተር ፕላን ፕሮግራም ተፈፃሚነት ግንባር ቀደም እንቅፋቶች መሆናቸውን ንቀት በተሞላበት መልኩ ከተናገሩ በኋላ እንደርሳቸው “የልክ ይገባል” ፉከራ ከሆነ እነዚህ በማስተር ፕላኑ ላይ ተቃውሞ ያላቸውና እንቅፋት የሆኑ በየደረጃው ያሉ የክልሉ ሰራተኞች የመጀመሪያ ልክ የሚገቡ ሰዎች ይሆናሉ::
ከኚሁ የዘመናችን ባለስልጣን የማስፈራሪያ ንግግር አንድ ልብ ብለን መገንዘብ ያለብን ነገር ያለ ይመስለኛል ይሔውም ለልማት ሳይሆን ለጥፋት ቆርጠው የተነሱ የህወሃት አባላት በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስ በከፍተኛ ስልጣን ከሚገኙ የክልሉ ተወላጆች እስከ ወረዳ ቀበሌ በሚገኙ የኦሮሞ ተወላጆች ያልጠበቁትን ከፍተኛ ተቃውሞ የተመለከቱበት ወቅት ከመሆኑ አንፃር ምናልባት ቀድሞ የታየው ተቃውሞ መልኩን ቀይሮ በተጠናከረ መልኩ ሊቀጥል ይችላል የሚል ስጋት ስለሚፈጠር እንደ አማራጭ ሊጠቀሙ የሚችሉበት ነገር በግለሰብም ደረጃ ሆነ ባጠቃላይ እንደ ህዝብ የማስፈራሪያና የማሸማቀቂያ ቃላትን በመወርወር ከወዲሁ የተቃውሞ ድምፆችን ለማቀጨጭ መሞከር ነው:: አቶ አባይ ፀሃዬ የፈፀሙትም ይሄንኑ ይመስለኛል::
ያለንበት ዘመን አንዱ ሌላውን ልክ እያስገባ የሚኖርበት ዘመን አይደለም:: ይልቁኑ የመብት ጥያቄ ለሚያነሳ ህዝብ ተገቢውን መልስ በመስጠት በሃገሪቱ ሰላምና መረጋጋት እንዲፈጠርና የህዝቦች መብት በእኩል አይን ሊከበር የሚችልበትን መንገድ መቀየስ እንጂ:: አቶ አባይ ፀሃዬ ይህ የገባቸው አይመስሉም:: ለ24 ዓመታት በህዝብ ጫንቃ ላይ ቁጭ ብሎ ህዝብን በንቀት አይን ሲመለከቱበት የነበረ ጊዜ አሁን ያበቃለት መሆኑን መረዳት ይኖርባቸዋል:: ብሶት ህውሃትን ብቻ ሳይሆን ሌላውንም የማይወልድበት ምክንያት ሊኖር አይችልምና::
Share this:https://www.gofundme.com/8bds2wgk