(Qeerroo News, Finfinnee, 16 May 2011)በአዲስ አበባ ከተማ ሚኒባስ ታክሲዎች በሚያስከፍሉት ታሪፍ ላይ ጭማሪ እንዲደረግና ትናንሽ ታክሲዎች ደግሞ በርቀት መለኪያ እየተጠቀሙ ክፍያ የሚጠይቁበትን ሁኔታ ለማመቻቸት መታቀዱን፣ የአገዛዙ ሹመኞች መግለጻቸውን ተከትሎ፣ በአዲስ አበባ ሁሉም ክፍለ ከተሞች የታክሲና አውቶብስ ፌርማታዎች ነዋሪዎች እጂግ ሲጨናነቁ መታየታቸውን ዘጋቢያችን ገለጸ::
የአዲስ አበባ ከተማ የታክሲ ስምሪት በቀጣና እንዲመደብ በተደረገ በስድስተኛ ቀኑ ከታክሲ አሽከርካሪዎች ተቃውሞ ገጠመው፡፡ በዚህም ምክንያት ስምሪቱ ሰኞ ማለዳ ተስተጓጐሎ ነበር፡፡ባለፈው ሳምንት ረቡዕ የተጀመረው የቀጣና ስምሪት የታክሲ ሾፌሮችንና ረዳቶችን እንዳላስደሰተ ይነገራል፡፡
የተዘረጋው የቀጣና ስምሪት አሠራር የትራንስፖርት ችግሩንም የሚፈታ አይደለም፡፡ ብዙ ሰዓት ያለሥራ እንድንቆም የሚያደርግ ነው ሲሉ የታክሲ ሾፌሮቹ ይከራከራሉ፡፡ በሌላ በኩል የአዲስ አበባ መንገድና ትራንስፖርት ቢሮ የቀጣና ስምሪት ችግር ፈቺ ነው፤ ችግሮች ካሉ በሒደት ይፈታሉ ብሏል፡፡ ችግሩ ሙሉ ለሙሉ ሳይፈታ የከተማው ሕዝብ በታክሲ እጥረት ምክንያት ሲጉላላ ያሳለፈ ሲሆን፣ ሰኞ ማለዳ ላይ ጭራሹኑ ከተማው በከፍተኛ የታክሲ እጥረት ተመቷል፡፡
‹‹ተገቢ ያልሆነ አድማ ነው፤ ጥቅማችንን ይጎዳል፤ የታክሲ ሾፌሮች የወሰዱት ተገቢ ያልሆነ ዕርምጃ ነው፤›› በማለት ለረጅም ዓመታት የታክሲ ባለንብረቶች ማኅበርን ሲመሩ የቆዩት አቶ ፍስሐ ማሞ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
በተለይ በአውቶብስ ተራ፣ በፈረንሳይ ለጋሲዮን፣ በቤላ፣ በአዲሱ ገበያና በአስኮ አካባቢዎች ከፍተኛ የታክሲ እጥረት የታየ ሲሆን፣ በሥራ መግቢያ ሰዓት የታክሲ አገልግሎት ባለመኖሩ ነዋሪዎች መጉላላታቸውን ያገኘናቸው መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡
በየትኛውም ጊዜና ሰዓት ታክሲ የተትረፈረፈባቸው የቦሌ ድልድይ፣ ሃያ ሁለት ማዞርያና ካዛንቺስ መስመር ሰኞ ማለዳ ከፍተኛ የታክሲ እጥረት ታይቶባቸው ነበር፡፡ በእነዚህ መስመሮች አንዳንድ ታፔላቸውን የነቀሉ ታክሲዎችን ማየት ችሏል፡፡
በገርጂ መብራት ኃይል አካባቢም የታክሲ እጥረቱ የተከሰተ ሲሆን፣ ትራንስፖርት ሲጠብቁ ከነበሩት ተገልጋዮች መካከል አንዳንዶቹ ወደ ቤታቸው ሲመለሱና ሌሎች ደግሞ በእግራቸው ሲጓዙ ታይተዋል፡፡ በሥፍራው የነበሩ ያነጋገርናቸው የታክሲ ተራ አስከባሪዎች እንደገለጹት፣ ታክሲዎቹ ወደ ገርጂ እንዲመጡ ስለሚገደዱና በማለዳ ደግሞ ወደ አካባቢው የሚሄዱ ተጓዦችም ባለመኖራቸው ያለምንም ሥራ ቆመው ወረፋ መጠበቁ አያዋጣም ብለዋል፡፡
ታፔላ ሳይለጥፉ 16 ተሳፋሪዎችን በመጫን ከቦሌ ድልድይ ወደ 22 ሲጓዝ የነበረ አንድ የታክሲ አሽከርካሪን ባነጋገርንበት ወቅት፣ የትራፊክ ፖሊሶች የሚያዩት ታፔላ ለጥፏል አለጠፈም የሚለውን በመሆኑ ትርፍ መጫኑ ምንም ችግር እንደሌለው ተናግሯል፡፡
አዲስ የተፈጠረውን የታክሲ ችግር አስመልክቶ አስተያየታቸውን እንዲሰጡት ዘጋቢያችን ያናገራቸው ነዋሪዎች፣ የአሁኑ የታክሲ ችግር ነጠላ ዜማ ደግሞ አዲስና ህብረተሰቡም ስለሌላ ነገር እንዳያስብ ማጥመጃ እንደሆነ እንደሚያምኑ ገልጸዋል።
አስተያየት ሰጪዎቹ ዘረኛው የወያኔ አገዛዝ በቅርብ ጊዜ የነጋዴውን ማህበረሰብ ከህዝቡ ጋር የማጣላት ሰፊ ዘመቻ ከፍቶ ሊሳካለት ባለመቻሉ አሁን ደግሞ ታክሲ አሽከርካሪና የታክሲ ባለሃብቶችን ከህብረተሰቡ ጋር በማናቆር በጋራ እንዳይቆሙ ለማድረግ የተጠነሰሰ ሴራ ነው ብለዋል።
አያይዘውም በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ኢትዮጵያ ውስጥ ህዝባዊ አመጽ ሊነሳ ይችላል የሚል ስጋት ያየለበት ዘረኛው የወያኔ አገዛዝ እያንዳንዱአን ቀዳዳ ለማድፈን ሌት ተቀን እየሰራ እንደሆነ ገልጸዋል።
በመጨረሻም ምንም አይነት አፈና ያድርግ ምንም አይነት ዘዴን ይቀይስ ኢትዮጵያ ውስጥ ህዝባዊ አብዮት መፈንዳቱ ፍጹም አይቀሬ እንደሆነ በርካታ ምልክቶች እየታዩ መሆናቸውን በመግለጽ አስተያየታቸን አጠቃለዋል።
በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ላይ 8,500 ሚኒባስ ታክሲዎች የሚገኙ ሲሆን፣ እነዚህ ታክሲዎች ሥራ አቁመው ይቅርና ሙሉ አቅማቸውን ተጠቅመው እንኳ ቢሠሩ፣ የከተማው የትራንስፖርት እጥረት አይቀረፍም ፡፡
Share this:https://www.gofundme.com/8bds2wgk