የመለስ ዜናዊ ፓርላማ ሰኔ 7 ቀን 2003 ዓ.ም. የኦሮሞ ነፃነት ግንባርን (ኦነግ)፣ ግንቦት 7: የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄን (ግንቦት 7)፣ እና የኦጋዴን ብሄራዊ ነፃነት ግንባርን (ኦብነግ) በሽብተኝነት መፈረጁ ተሰምቷል።
በሽብርተኝነት የተፈረጁት የኦሮሞ ነጻነት ግንባርና የኦጋዴን ብሄራዊ ነጻነት ግንባር የተከሰሱት፤ መለስ ዜናዊ እራሱ የሚመራው ህዝባዊ ወያኔ ሃሪነት ትግራይ በአማርኛ አጠራሩ የትግራይ ነጻ አውጪ ግንባር በ17 አመት ጸረ ደርግ የትጥቅ ትግል ወቅት በተጠቀመባቸው የትግል ስልቶች በመጠቀማቸው እንደሆነ የውሳኔ ሰነድ ይፋ አድርገዋል።
በሽብርተኝነት ከተፈረጁት 5 ድርጅቶች አንዱ፣ኦነግ ነው ፡፡ እንደ ኢሕአዴግ ወያኔ ፓርላማ ከሆነ፣ ከ1987 እስከ 2ዐዐዐ ዓ.ም ድረስ 1ዐ6 የሽብር ጥቃቶችን ፈፅሞ፣ 56 ዜጎች ሞተዋል፡፡ 284 ደግሞ ከባድና ቀላል የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡ ከ2ዐዐዐ በኋላ ስላለው ጊዜ ምንም የተባለ ነገር የለም፡፡
ኦነግ የተቋቋመው በ1967 ዓ.ም ነበር፡፡ ዘንድሮ 36 ዓመታትን አስቆጠሯል፡፡ 17ቱ በደርግ ዘመን ጦርነት ላይ ነበር፡፡ በብርጌድ ደረጃ እስከመዋጋት ደርሶ ነበር፡፡ አንድም ጊዜ ግን፣ ከተማ ውስጥ ፈንጂ በማፈንዳት ተወንጅሎም ታምቶም አያውቅም፡፡
አሸባሪ ብሎ ድርጅቶችን መሰየም ውድቀታቸው የተቃረበ አምባገነኖች የመጨረሻ ቀናቸው ሲደርስ ባለፉት ሁለትና ሶስት ወራት እንዳየነውና እንደሰማነው ተቃዋሚዎቻቸውን ወይንም ዴሞክራሲያዊ ስርአትን ለሚፈልጉ የለውጥ አራማጆች በሙሉ የሚሰጡት ተቀጽላ መሆኑን ዓለም ያወቀው ጉዳይ ነው:: ሙባረክ ተቃዋሚዎቹን አሸባሪ ሲል ነበር፣ ጋዳፊ ገና ህዝቡ ሰልፍ ሲወጣ ይህን እያደረገ ያለው አልቃይዳ ነው፣ ድረሱልኝ እያለ ይጮህ ነበር፣ የመን ላይም የሚታየው ተመሳሳይ ሁኔታ ነው::
ኦነግን ያገለለ የተሟላ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ሊኖር አይችልም፡፡ የኦነግን ችግር መፍታት የሚቻለው በፖለቲካ ነው፡፡ ለፖሊስም ሆነ ለሠራዊቱ የሚተው አይደለም፡፡ በሽብርተኝነት በመፈረጅ በሚሊዮኖች እንደሚቆጠሩ ከሚገመቱት ደጋፊዎቹ ልብ ውስጥ ፈንቅሎ ማውጣት አይቻልም፡፡ ትርፉ፣ በሰላማዊው በር ላይ በርን መዝጋት ብቻ ነው የሚሆነው፡፡
ከኦነግ ሌላ፣ በሽብርተኝነት የተፈረጀው ኦጋዴን ብሄራዊ ነጻነት ግንባር ኦብነግንም በአዋጅ ማጥፋት አይቻልም፡፡ እዚህም ያለው የፖለቲካ ችግር ነው፡፡ መፍትሄውም ፖለቲካዊ ብቻ ነው፡፡ ፍረጃው ሀገሪቷን ወደዚያ አያቀርባትም፡፡ ደርግ፣ በኤርትራ የሰራውን ስህተት ኢሕአዴግ በኦጋዴን ሊደግመው አይገባም፡፡ የኢትዮጵያ አንድነት ታላቁ ፈተና በኢትዮጵያ ሱማሌ ክልል ውስጥ ተቀብሮ ይገኛል፡፡ መፍትሔው፣ ጥበብን፣ ብልሃትን፣ ብስለትን ይጠይቃል፡፡ ኃይል ቦታ የለውም፡፡ በኤርትራ ተረጋግጧል፡፡
የፈደራል ጉዳዮች ሚንስቴርና የመለስ ዜናዊ አማካሪ የሆነው አባጸሃይ ከወራት በፊት ከኦጋዴን ብሄራዊ ነጻነት ግንባር ጋር የሰላምና የእርቅ ስምምነት ተፈርሞአል ፤ በዚህም ምክንያት ከአሁን ቦኋላ ኦብነግ የሚባል ድርጅት የለም በማለት ለህዝብ ተወካዮች ተብዬው ምክር ቤት ሪፖርት አቀርቦ እንዳልተጨበጨበ በራሳቸው አንደበት ገድለው የቀበሩትን ድርጅት ከመቃብር አስነስተው ” ለብሄራዊ ጸጥታ አስጊ በመሆኑ በሽብርተኝነት ፈርጀነዋል ” ማለታቸው አገራችን በምን አይነት ሂሊና ብሶች ስብስብ እየተመራች እንደሆነ ሌላ ተጨማሪ ማስረጃ ሆኖአል።
የወያኔ የህዝብ ተወካዮች አጸደቁት በተባለው ድርጅቶቹን በሽብርተኝነት የፈረጀ ሰነድ ላይ “ግንቦት 7 በቀድሞ የቅንጅት ነውጠኛ አመራሮች የተቋቋመ ድርጅት ነው” ካለ ቦኋላ “እነኚህ አመራሮች ህገ መንግስታዊ ሥርዓቱን በኃይል ለመናድ መሞከራቸው በፍ/ቤት ተረጋግጦና አምነው በድርጊታቸው ተጸጽተው ከእንግዲህ ወዲያ ህገ መንግስቱን እንደሚያከብሩና እንደሚያስከበሩ ቃል ገብተው ይቅርታ ይደረግላቸው ዘንድ መንግስትና ህዝብ በይፋ በመጠየቃቸው ይቅርታ ተደርጎላቸው ከእስር እንዲፈቱ መደረጉ ይታወቃል፡፡ ሆኖም በይቅርታ ከእስር ከተፈቱ በኃላ ህገ መንግስታዊ ሥርዓቱን በማናቸውም መንገድ ለማፍረስ አቅዶ የሚንቀሳቀስ ግንቦት 7 የሚል ቡድን ወይም ድርጅት አቋቋሙ፡፡ ብሎአል።
በመቀጠልም “ድርጅቱ ዓላማዬ ብሎ በይፋ ያወጀው ” ሁሉን አቀፍ ትግል ” በመጠቀም አሁን ያለውን መንግስታዊ ሥርዓት ማፍረስ ሲሆን በተለይ ደግሞ በከተሞች አካባቢ በመሰረተ ልማት ተቋማት ፣ በከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት ላይ ሽብርና ግድያ መፈጸም እንዲሁም የከተማ አመጽ ማቀጣጠል የትጥቅ ትግል ማካሄድ እና ከማናቸውም ጸረ ኢትዮጵያ መንግስት አቋም ካላቸው ድርጅቶችና ሀገሮች ጋር በጋራ መስራት ነው”፡ በማለት የግንቦት7 መፈጠር ያሳደረበትን ስጋትና ጭንቀት ገልጾአል፡፡
እነ ዶ/ር ብርሃኑን የኢሕአዴግ መሪዎች በደንብ ያውቋቸዋል፡፡ በየቡናቤቱ ፈንጂ ያጠምዳሉ ብለው እንደማይጠረጥሯቸው መገመት አያስቸግርም፡፡ በምዕራብ ሀገራት ለረዥም ግዜ የኖሩት የግንቦት 7 መሪዎች፣ ለሰብአዊ መብት ደንታ የሌላቸው ሽብርተኞች ሆነው መቀመጣቸው ተዓማኒነቱ እምብዛም ነው፡፡ ከዚያ ይልቅ፣ እውነታው ያለው እነዚህ ሰዎች ወደ ሀገራቸው ተመልሰው የፖለቲካው አካል መሆን ለእውነተኛ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት እውን መሆን አስፈላጊ መሆኑ ላይ ነው፡፡ የኢሕአዴግ መሪዎች፣ እየመረራቸውም ቢሆን ከዚህ እውነታ ጋር የመጋፈጥ ኃላፊነት አለባቸው፡፡ አሁን የተያዘው መንገድ አያዋጣም፣ አያዛልቅም፡፡
የኢሕአዴግ መሪዎች ሆይ! ፖሊስና ወታደር የፖለቲካ ችግር ፈቺዎች አይደሉም፡፡ የሀገሪቱን የዲሞክራሲ ፈተና የእነሱ ዕዳ አድርጎ ማስቀመጥ ከደርግ ስህተት አለመማር ነው፡፡ ችግሩን ከምንጩ ማድረቅ ያስፈልጋል፡፡ ምንጩ ደግሞ ፖለቲካ ነው፡፡ ውንጀላውን ትታችሁ ተደራደሩ፡፡ ለሀገር የሚበጀው ብቸኛው መንገድ ድርድርና እርቅ ነውና፡፡
Share this:https://www.gofundme.com/8bds2wgk