ኢትዮጵያ ዘርፍ ምክር ቤት እና የኦሮሚያ ዘርፍ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ከዱ።

ONN- ዜና
ኢትዮጵያ ዘርፍ ምክር ቤት እና የኦሮሚያ ዘርፍ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ከዱ። በአንድ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣን ከተመራ የልዑካን ቡድን ጋር ዘርፍ ምክር ቤቱን በመወከል ወደ አውስትራሊያ ከተጓዙ በኋላ፣ ሌሎች የልዑካን ቡድን አባላት ሲመለሱ እርሳቸው መቅረታቸውን ምንጮች ገልጸዋል፡፡

ከኢትዮጵያ የንግድ ልዑካን ጋር ወደ አውስትራሊያ ተጉዘው የነበሩት የኢትዮጵያ ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት አውስትራሊያ ከሄዱ በኋላ ሪፖርት ሳያደርጉ አንድ ወር ማስቆጠራቸው ጥያቄ አስነሳ፡፡ በዚህም ምክንያት ቼክ ላይ የሚፈርም በመጥፋቱ ችግር መፈጠሩን ምንጮች ገልጸዋል፡፡

በቅርቡ በተካሄደ አወዛጋቢ ምርጫ የኢትዮጵያ የዘርፍ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሆነው የተመረጡት አቶ ኢያሱ ሞሲሳ፣ በአንድ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣን ከተመራ የልዑካን ቡድን ጋር ዘርፍ ምክር ቤቱን በመወከል ወደ አውስትራሊያ ከተጓዙ በኋላ፣ ሌሎች የልዑካን ቡድን አባላት ሲመለሱ እርሳቸው መቅረታቸውን ምንጮች ገልጸዋል፡፡

እንደ ምንጮች ገለጻ ከሆነ አቶ ኢያሱ መመለስ የነበረባቸው ከሦስት ሳምንታት በፊት ነበር፡፡ የጉዞ ፕሮግራሙ ካለቀ በኋላ ሪፖርት ሳያደርጉ በመቆየታቸው፣ በዚያው ቀርተዋል የሚል ድምዳሜ ላይ ተደርሷል፡፡ በተለይ ከተረከቡት ኃላፊነት አንፃር ውክልና ሳይሰጡ አንድ ወር መቆየታቸው የጽሕፈት ቤቱን እንቅስቃሴ እንዳስተጓጎለ ምንጮች ገልጸዋል፡፡

አቶ ኢያሱ ከኢትዮጵያ ዘርፍ ምክር ቤት በተጨማሪ የኦሮሚያ ዘርፍ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ናቸው፡፡ በዚህም ምክንያት ለሁለቱም ዘርፍ ምክር ቤቶች ጽሕፈት ቤቶች የሚያስፈልግ ገንዘብ ለማንቀሳቀስ አለመቻሉም ታውቋል፡፡ ለሁለቱ ምክር ቤቶች አንደኛው ቼክ ፈራሚ አቶ እያሱ መሆናቸውን የሚገልጹት ምንጮች፣ በቼክ ፈራሚ ዕጦት ለሠራተኞች የሚከፈል ደመወዝ ማውጣት እንዳልተቻለም አስረድተዋል፡፡

በኢትዮጵያ ዘርፍ ምክር ቤት አሠራር መሠረት ፕሬዚዳንት ከሌለ ምክትሉ ተተክቶ እንደሚሠራ ቢታወቅም፣ ምክትል ፕሬዚዳንቱ አቶ ልሳኑ በለጠም ወደ አውስትራሊያ መሄዳቸው የተለመደውን አሠራር እንዳስተጓጎለው ምንጮች አክለዋል፡፡ አቶ ልሳኑ ወደ አውስትራሊያ የተጓዙት የልዑካን ቡድኑ ፕሮግራም ከተጠናቀቀ በኋላ በመሆኑ ክስተቱን አነጋጋሪ አድርጎታል፡፡

የኢትዮጵያ ዘርፍ ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት አንድ ኃላፊ በጉዳዩ ላይ አስተያየት እንዲሰጡ ተጠይቀው ለጊዜው አስተያየት ከመስጠት ተቆጥበዋል፡፡ በሌላ በኩል ሁሉም ተጓዦች የተሰጣቸው ቪዛ እስከ ዲሴምበር 20 ቀን 2017 በመሆኑ ቀርተዋል ወይም አይቀሩም ለማለት፣ የቪዛ መጠናቀቂያ ጊዜውን መጠበቅ ያስፈልጋል የሚሉም አሉ፡፡

ነገር ግን ለጽሕፈት ቤቱ እንቅስቃሴ ቼክ ፈራሚ ጭምር መሆናቸው እየታወቀ ለአንድ ወር ሪፖርት አለማድረጋቸው የጽሕፈት ቤቱን ሥራ በማስተጓጎሉ፣ ቀሪዎቹ የቦርድ አባላት በቀጣይ ሳምንት አስቸኳይ ስብሰባ ለመጥራት እየተዘጋጁ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡ የጽሕፈት ቤቱ የሥራ ኃላፊዎች ግን ስለዚህም ጉዳይ አስተያየት ለመስጠት እንቸገራለን ብለዋል፡፡

አቶ እያሱ የኦሮሚያ ክልል ዘርፍ ምክር ቤትና የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሲሆኑ፣ አቶ ልሳኑ ደግሞ የአማራ ክልል ዘርፍ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሆነው በማገልገል ላይ ናቸው::

 

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s