ስንብት – ለኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት!

ጂቱ ለሚ

የካቲት 15 ቀን 2015ዓም

barruuያ ሰዉ በጣም ደስተኛ ነበር። ዛሬም ብዙዎች በየቀኑና በየቦታው 26ቱን ማይልስ በመሮጥ የዚያን ሰዉ ደስታ ያስቡታል። ሆኖም ግን ስንቶች የዚህን ታሪካዊ ክስተት ትርጓሜና አመጣጥ በዉል እንደሚገነዘቡ መገመቱ ያስቸግር ይሆናል። ያ ሰዉ ግን ስለምን እንደዚያ እንደሚሮጥ በሚገባ ያዉቀዉ ነበር። ምክንያቱም በጦርነት የታዳከመ ሰዉነቱ ሳይዝል 26ቱን ማይልስ በብቃት ሮጦ እጅግ ታላቅ  የድል ዜናን ለወገኖቹ ካደረሰ በኋለ እስከ ወዲያኛዉ ኣርፈዋልና!

ዘመኑ ከክርስቶስ ልደት በፊት 490 ነዉ። ከታላቁ የፐርሽያ (Persian) ኢምፓየር ታላቅና ኃያል ሠራዊት ተንቀሳቀሰ። በግዝፈቱም፣ በታጠቀዉ መሣሪያ ዘመናዊነትና በስልጠናዉ ደረጃም የዘመኑ ዓለም ከደረሰበት ዝማኔ በላይ በእጅጉ የረቀቀ ነዉ። በዚህ ላይ ደግሞ ሽንፈትን የማያዉቅ የደረሰበትን ሁሉ ጠራርጎ የሚሄድ “የንጉሦች ንጉስ ፣ የጌቶቹ ጌታ” የተባለለት የታላቁ ንጉስ ዳሪዮስ ጦር ነዉ። እናም የቀደመ የድል ታሪኩን እያስታወሰ ታላቅነቱን እያሰበ በኩራት ተንቀሳቅሷል። ዓላማዉ ደግሞ ከወዲያ ያለዉን ሉዓላዊ መሬት በሃይል ጨፍልቆ መያዝ ነዉ። ይህ ለንጉሡ ጦር ቀላልና ተራ  ነገር ነው። እናም ለዉጊያ ስልት የመረጠዉን ረባዳዉን የመራቶን ሜዳ በቅድሚያ ተቆጣጥሮ ህልሙ የሆነችው የአቴንስ ከተማ ላይ ሆነዋል።

ከወዲያኛዉ ግንባር ደግሞ በዚህ ግዙፍ ኃይል እምብዛም ግምት ያልተሰጠዉና ግዛቱን ላለማስነጠቅ ብቻ በኣራት እጥፍ የሚበልጠውን ታላቁን ጦር የተጋፈጠ የግርክ ሠራዊት ግንባር ግንባር መፋጠጥ ይዘዋል። እንዳለመታደል ሆኖ ለክፉ ቀን ተስፋ የተጣለባቸዉ የጎረቤት እስፓርታ ሰዎች እንኳ ሀይማኖታዊ በዓላቸዉን እያከበሩ ስለሆነ ሙሉ ጨረቃ በሰማይ ላይ እስከምትታይ ድረስ ወደ ጦር እንደማይገቡ ምላሽ ሰጥተዋል። እናም የቱን ያህል ከባድ ቢመስልም የአቴንስ ሰዎች ሀገራቸዉን የመከላከሉን ግዴታ ብቻቸዉን ሊሞክሩት ነዉ። ፍጥጫዉ ለዘጠኝ ቀናት ዘልቋል።

Good bye Empire – Jiituu

1 thought on “ስንብት – ለኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት!

Leave a comment