
(ቄሮ – የኦሮሞ ወጣቶች) ባለፈው ረቡዕና ሐሙስ በአዳማ ዩኒቨርሲቲ በተማሪዎች መመገቢያ አዳራሽ ውስጥ የተመገቡ 1500 ያህል ተማሪዎች በጠና ታመሙ፡ተማሪዎች ዓርብ ባስነሱት ተቃውሞ ከፖሊስ ጋር መጋጨታቸውንና ግቢው በፖሊስ ጥበቃ ሥር መዋሉ ታውቋል፡፡

Adama Uni Students up rising
በዩኒቨርሲቲው የሚገኙ የቄሮ ምንጮች እንደገለጹት፣ ረቡዕ ተማሪዎቹ ምሳ ከበሉ በኋላ ወደ 11 ሰዓት ገደማ በርካታ ተማሪዎች መታመም ጀመሩ፡፡ የሕመሙ ምልክቶች ራስ ምታት፣ ቁርጠትና ራስን እየሳቱ መውደቅ ሲሆኑ፣ በሁሉም ታማሚ ተማሪዎች ላይ ተመሳሳይ ምልክቶች ታይተዋል፡፡
አንዳንድ ያነጋገርናቸው የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች እንደገለጹት ከሆነ ደግሞ፣ ተማሪዎቹ ወደላይ አያስመልሳቸውም ወይም የሆድ ሕመም ምልክት አይታይባቸውም፡፡ ነገር ግን ራሳቸው ክፉኛ መታመሙን የሚገልጹና ራሳቸውን ስተው የሚወድቁ በርካቶች ነበሩ፡፡
ረቡዕና ሐሙስ በጠቅላላው 1500 ያህል ተማሪዎች የታመሙ ሲሆን፣ በዩኒቨርሲቲው ቅጥር ግቢ በሚገኘው የጤና ማዕከልና በአዳማ ሆስፒታል የሕክምና ዕርዳታ እንደተደረገላቸው ለማወቅ ተችሏል፡፡
ተማሪዎቹ ከበሽታው በፍጥነት ማገገማቸውን የገለጹት ምንጮች፣ በምግብ መመረዙ የተጠቁት ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲው ከሚገኙ አራት የተማሪዎች መመገቢያ አዳራሾች በአንደኛው አዳራሽ የተመገቡት ብቻ ናቸው፡፡
የዩኒቨርሲቲው ምንጮች ክስተቱን የተለመደው ዓይነት የምግብ መመረዝ ይበሉት እንጂ፣ ተማሪዎቹ ግን የተለምዶው የምግብ መመረዝ ሳይሆን ከኬሚካል ጋር የተገናኘ ችግር ሳይሆን እንደማይቀር መገመቱን ይገልጻሉ፡፡
ለታማሚዎቹ ተማሪዎች የሕክምና ዕርዳታ የሰጡት ሐኪሞች በሽታው የምግብ መመረዝ እንደሆነ ያረጋገጡ ሲሆን፣ የምግብ ናሙናዎች ለኢትዮጵያ የሥነ ምግብና የጤና ምርምር ኢንስቲትዩት (ፓስተር) እንደተላኩ ለማወቅ ተችሏል፡፡
በምግብ መመረዙ የተቆጡ የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች ተሰብስበው ከግቢ በመውጣት ከተማ ጎዳናዎች ላይ በመዘዋወር ተቃውሟቸውን ለመግለጽ ሲሞክሩ፣ የዩኒቨርሲተው አስተዳደር የአዳማ ከተማን ፖሊስ በመጥራት ተማሪዎቹ ከግቢ እንዳይወጡ አድርጓል፡፡
አብዛኞቹ የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች በተለይ በአዲስ አበባና በአካባቢዋ ወደሚገኙ ቤተሰቦቻቸው መመለሳቸውንና ግቢ ውስጥ የቀሩት ግን በፖሊስ ጥበቃ ሥር እንደሚገኙ ለማወቅ ተችሏል፡፡
የአዳማ ዩኒቨርሲቲ የበላይ ጠባቂና ቦርድ ሊቀመንበር ጁነዲን ሳዶ ዓርብ ከሰዓት በኋላ በፖሊስ ጥበቃ በዩኒቨርሲቲው ቅጥር ግቢ ተገኝተው ተማሪዎቹን ለማነጋገር ሲጥር ከፍተኛ ውጥረት ይታይ እንደነበር ለማወቅ ተችሏል፡፡
ተማሪዎቹ ከግቢ ለመውጣት ከፖሊስ ጋር በፈጠሩት ግብግብ ለፖሊስ ቆመጥ መዳረጋቸውን የዓይን እማኞች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ ተማሪዎቹ በግቢው ውስጥ የነበሩ የተወሰኑ የዩኒቨርሲቲውን ተሸከርካሪዎች መስታወት በድንጋይ ሰባብረዋል፡፡ በተጨማሪም ዓርብ የዩኒቨርስቲውን ሕንፃዎች መስተዋት መሰባበራቸውን አስረድተዋል፡፡