የኢህአዴግ መንግሥት የደህንነት ሰዎች በቅርቡ በቡራዩ በአዲስ አበባ እና በዱከም ማረሚያ ቤቶች በእስር ላይ ካቆያቸው ከ60 በላይ የኦህዴድ ባለሥልጣናት የግል ካዝና ከ165 ሚሊዮን ብር በላይ መውረሳቸውን የዜና ምንጮቻችን ገለጹ፡፡ የሰበታ ከተማን ላለፉት ስምንት ዓመታት በከንቲባነት ያስተዳደሩት አቶ ሽመልስ ሀሰኖ፣ እንዲሁም ከሰበታ ከተማ ሰራ አስኪያጅ የነበሩ ግለሰብ እና ከሌሎች በእስር ላይ ከሚገኙ ከሌሎች ባለስልጣናት ነው ገንዘቡ የተወሰደው።
አቶ ሽመልስ ሀሰኖ በቡራዩ ወህኒ ቤት ቆይታቸው የጠበቀ “ምርመራ” ተደርጎባቸዋል።አንድ የአዲስ ነገር ምንጭ እንደተናገረው በእስር ላይ የሚገኙ አንዳንድ የቀድሞ የኦህዴድ የበታች ባለስልጣናት “ ከግርፋት ብዛት ባለፉት ሁለት ወራት የካዱትን የሙስና ወንጀል በማመን ገንዘቡን ለመንግስት መልሰዋል” ብለዋል ፡፡
አሁንም “በሙስና የተጠረጠሩ” በርካታ የኦሮሚያ ክልል የወረዳ፣ የዞንና የክፍለ ከተማ የኦህዴድ- ኢህአዴግ ባለሥልጣናትና ኃላፊዎች በቁጥጥር ሥር በመዋል ላይ እንደሚገኙ ምንጮቻችን ገልጸውልናል፡፡
አቶ አባዱላ ገመዳ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት ኾነው በቆዩባቸው አምስት አመታት በክልሉ ተወዳጅነት ነበራቸው። ይህ በአቶ መለስ ዜናዊ አልተወደደም። የአዲስ አበባ የፖለቲካ ታዛቢዎች አቶ አባዱላ የምክትል ጠቅላይ ሚኒስቴርነትን ቦታ እንደሚያገኙ ታስቦ የነበረ ቢኾንም አፈጉባኤ ተደርገው ከሚዲያ እይታ ገሸሽ እንዲሉ ተደርገዋል።
የኢህአዴግ/ህወሀት ሰዎች አቶ አባዱላን በኦሮሚያ ክልል ውስጥ “ኔትዎርክ “ በመዘርጋት እና የተክለ ሰብእና ግንባታ/ከልት/ ይከሷቸዋል። ይህ ኦህዴድ ላይ ያነጣጠረው “የ ሙስና” ዘመቻ የአባዱላን ደጋፊዎች የመመንጠር ሥራ አድርገው የሚወስዱትም አሉ። የአዲስ አበባ ከንቲባ አቶ ኩማ ደመቀሳ እና የኦህዴድ ሊቀመንበር አቶ አለማየሁ አቶምሳ ምንጠራውን እና እስሩን እያስፈጸሙ ነው።
በሃብት ምዝበራው ወንጀል የተጠመደው ዘረኛው እና አምባገነኑ መለስ ዜናዊ የአገዛዝ ዘመኑን ለማራዘም ከሌሎች ብሄር ብሄረሰቦች በትናንሽ ጥቅማ ጥቅሞች እና መደለያ በዙሪያው ያሰባሰባቸውን አንዳንድ ግለሰቦች በተለያየ ውንጀላ የማስወገድ ተግባሩን እየገፋበት እንደሆነ በዚህም ምክንያት አባዱላ ገመዳ የወቅቱ ተረኛ እንደሆነ ምንጮች ለዝግጅት ክፍላችን አስታወቁ።
ለረጅም ጊዜ የኦሮሚያ ክልልና የኦህዴድ ፕሬዝዳንት በመሆን በኦሮሞ ህዝብ ላይ የሚደርሰውን የአጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ ሲያስተገብር የቆየው አባ ዱላ ገመዳ ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ ከመለስ ዜናዊ ጋር በገባበት አለመግባባት ግልጽና ስውር ተጽዕኖዎች እየደረሰበት እንደሚገኝ ለግለሰቡ ቅርበት ያላቸው ምንጮች አረጋግጠዋል።
እንደ የኦሮሚያ አካባቢ ምንጮች መረጃ በአባዱላና በመለስ ዜናዊ መካከል የነበረውን አለመግባባት የተባባሰው ሸክ አላሙዲን በኦሮሚያ ክልሉ በስሙ ይዞት የነበረውን ሰፊ የልማት ቦታ ለረጅም ጊዜ ምንም የግንባታ ሥራ አልሰራበትም በማለት እንዲወረስ ካስደረገና በኦህዲድ ሥር የሚተዳደረው የድንሾ ንግድ ድርጅት በጫት ንግድ ገቢያ የነበረውን ድርሻ የመለስ ዜናዊ ባለቤት አዜብ መስፍን ለመቆጣጠር ጣልቃ ስትገባ ለማስቆም ከተፍጨረጨረ ቦኋላ እንደሆነ ለማወቅ ተችሎአል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከመለስ ዜናዊ በቀጥታ የሚተላለፈው ቀጭን ትዕዛዝ ክልላችንን ይጎዳል በማለት ቅሬታ ያሰሙ ከከፍተኛ አስከ ተራ የኦህዲድ አባላት ያሉ ግለሰቦች በሙስናና በኦነግ አባልነት ተወንጅለው ከርቼሌ እንደወረዱ በተለያየ ሚዲያ መዘገቡ ይታወሳል ። አባዱላ ገመዳ በትርፍነት ከተመራው የከተማ ቦታ አንዱን በቅርቡ ለድርጅቱ ኦህዲድ አውርሶ እንደነበረ የሚያስታውሱ ምንጮቻችን በተጨማሪ ሰሞኑን በአዲስ አበባ ቦሌ ወሎ ሰፈር አካባቢ ያስገነባውን ባለ አራት ፎቅ መኖሪያ ቤቱን በሙስና ሰበብ መነጠቁን ገልጸዋል። የአባዱላ ጣጣ በዚህ ሳያበቃ ተጨማሪ ክስ በጸረሙስና ኮሚሽን በኩል ሊመሰረትበት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የደረሰን መረጃ ያመለክታል።
አባዱላ ገመዳ በቅርቡ ለህክምና ሰበብ ወደ ጀርመን መጥቶ እንደነበርና ከመለስ ዜናዊ የሚደርስበትን ውርደት ለመሸሽ ጥገኝነት የመጠየቅ ሃሳብ እንደነበረው ነገር ግን በስደት ህይወት ውስጥ ያለውን ውጣ ውረድ የመቋቋም ፍርሃት ገብቶት ሃሳቡን እንደቀየረና በመጣበት እግሩ እንደተመለሰ ተያይዞ የደረሰን መረጃ አረጋግጦአል።
ለመለስ ዜናዊ ባላቸው ታማኝነት ብቻ ዕውቀት እና ችሎታቸው በማይመጥናቸው የስልጣን ማማ ላይ ከተፈናጠጡት የጄሌ ድርጅቶች መሪዎች መካከል ከመለስ ዜናዊ የሚደርስባቸውን ውርደት ለማስቆም የምቾት ህይወታቸውን አሳልፈው የሰጡ ብዙ አይደሉም። የቤንሻንጉል እና ጉሙዝ ክልል ፕሬዝዳንት የነበረው ያረጋል አይሸሹም ከሁለት አመት በፊት በስደት ካናዳ ከደረሰ ቦኋላ ወዲያው ተጸጽቶ ይቅርታ በመጠየቅ ለመለስ ዜናዊ መልሶ እጁን እንደሰጠ ይታወሳል።