የወያኔ አገዛዝ መሰረታዊ የሆነ በኢንተርነት መረጃ የማግኘት ነጻነትን በመገደብ ከሳራ በታች ካሉት አገሮች ብቸኛ እንደሆነ ተቀማጭነቱ በአሜሪካን አገር በዋሽንግተን ዲስ የሆነው እና በዲሞክራሲ፤ በፖለቲካ ነጻነትና የሰብዓዊ መብትቶች ዙሪያ ላይ በአለም አቀፍ ደረጃ ምርምር የሚያደርግ ፍሪደም ሃውስ ሰሞኑን ባወጣው አመታዊ ሪፖርት ከሰሰ።
እንደፊሪደም ሃውስ ሪፖርት 85 ሚሊዮን የሚገመት ህዝብ በሚኖርባት ኢትዮጵያ የኢንተርነት ስርጭት ከዜሮ ነጥብ አምስት በታች ላይ የሚገኝ ነው። በዚህ ከቁጥር በማይገባ ስርጭ ላይ አገዛዙ የኢንተርነት ግንኙነቶችን ሳንሱር በማድረግ እና የፖለቲካ ክርክሮች፤ ውይይቶች ወይም አስተያየቶች የሚካሄዱባቸውን ድህረ ገጾች ጨርሶኑ በአገር ውስጥ እንዳይታዩ የመዝጋት የአፈና እርምጃ ይወሰዳል።
በኢትዮጵያ ቴሌኮሚኒከሸን አገልግሎት እንቅስቃሴ ውስጥ ጉልህ ድርሻ ያላት ቻይና፤ አገዛዙ ኢንተርኔትንና የሳታላይት ሞገዶችን ለመጥለፍ በሚያካሂደው ዘመቻ ዘመናዊ መሳሪያዎችን በማቀበል ብቸኛዋ ተባባሪ አገር እንደሆነች ሪፖርቱ አክሎ አጋልጦአል።
የአለም አቀፍ ቴሌኮሚኒኬሽን ድርጅት ባለፈው አመት ባካሄደው አለም አቀፍ ጥናት በኢትይጵያ ውስጥ ለኢንተርነት አገልግሎት የሚከፈለው ዋጋ ከዜጎች ወርሃዊ ገቢ ጋር ሲነፃጸር በአለም እጅግ ውድ ከሚባሉት ተርታ ይገኛል ያለው የፍሪደም ሃውስ ሪፖርት የዋጋውን ንረት በንፅጽር ለማሳየት ከፍተኛ የመረጋጋት ችግር ካለባቸው የመካከለኛው አፍሪካ አገሮች ተርታ እንደሚገኝ ገልጾ መንግሥት አልባ የሆነቺው ሱማሌ፤ ጎሬቤት አገር ጁቡቲ ፤ ኬንያና ሱዳን ከአገራችን በተሻለ ደረጃ ላይ እንደሚገኙ ከዘገባው መረዳት ተችሎአል።
እንግሊዝ አገር የሚገኘው የማንቺስተር ዩኒቨርሲት የትምህርት ክፍል ባለፈው የፈረንጆች አመት 2010 ባካሄደው ጥናት በአዲስ አበባ ውስጥ ብሮድ ባንድ በሚባለው የኢንቴርነት አገልግሎት አንድ ሰው የኢሜል መልዕክቱን ከፍቶ ለማዬት ከ6 ደቂቃ በላይ ጊዜ እንደሚፈጅበት ገልጾ የኢንተርኔት ፍጥነት እንዲህ እንዲዘገይ የሚደረገው ሆን ተብሎ አንደሆነ አጋልጦአል።
አገዛዙ ሊደርስባቸው በማይችልባቸው የውጪ አገሮች የሚኖሩ የዲያስፖራው ኮሚኒቲ ስለአገራቸው ፖለቲካ ጉዳይ የሚለዋወጡትን አስተያየቶች አቅጣጫ ለማሳት እና ለመንግሥታቸው እጅግ ቀናና በጎ የሆኑትን አስተያየቶች በምላሽ መልክ ለመስጠት በቋሚነት የሚሠሩ ደመወዝ የሚከፈላቸው ሰዎች መመደባቸውን ፍሪደም ሃውስ መረጃ እንዳለው በ2010 አመታዊ ሪፖርቱ አክሎ ገልጾአል።
የወያኔ አገዛዝ በኢንቴርኔት አማካኝነት የሚተላለፉ ማናቸውንም አይነት ይዜት ያላቸው በድምጽ እና በቪዲዮ የሚተላለፉ መልዕክቶችን ሁሉ እንደዘጋ ያጋለጠው ይህ የፍሪደም ሃውስ አመታዊ ሪፖርት ከውጪ ወደ አገር ቤት የሚተላለፉ ሬዲዮኖችን በሙሉ እንደሚያፍን ለዚሁም መለስ ዜናዊ የአሜሪካ ድምጽ የአማሪኛ አገልግሎትን ለማፈን እንደተዘጋጀ በአደባባይ የሰጠውን የራሱ ቃል በማስረጃነት አቅርቦአል።