(Qeerroo News, Finfinnee, April 17, 2011) ኢህአዴግ በመላ አዲስ አበባ የደህንነት እና የጸጥታ ጉዳይ ላይ የሚያተኩር ስብሰባ አደረገ፤ ልዩ ልዩ የሰላምና የልማት ኮሚቴዎችንም በአዲስ መልክ አዋቅሯል፡፡
በሕዝባዊ ውይይቱ ላይ ከፌዴራል ፖሊስ የተወከሉ ባለሥልጣናት በአሥሩም ክፍለ ከተሞች በመገኘት ወላጆች ልጆቻቸውን ተገቢ ባልሆኑ ቦታዎችና እንቅስቃሴዎች ላይ እንዳይሳተፉ እንዲቆጣጠሩ ማስጠንቀቂያ ሰጠ።
በአዲስ አበባ አሥሩም ክፍለ ከተሞች አዳራሾች ባካሄደው ሕዝባዊ ስብሰባዎች ላይ የኢህአዴግ አመራር አባላት የተገኙ ሲሆን ከወጣት ማህበራት፣ ከሴቶች ሊግ፣ ከጎበዝ ተማሪዎች፣ የመንግሥት ሠራተኞች እና ተደማጭ የአካባቢ ሰዎችንና ሽማግሌዎችን እንዲሁም የአካባቢው እድሮች አመራር አባላትን ያካተተ ልዩ ልዩ ከሚቴዎችን በአዲስ መልክ አቋቁሟል፡፡
በስብሰባው ላይ የኢህአዴግ አመራር አባላት የአምስት ዓመቱን የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድንና በቅርቡ መንግሥት ይፋ ያደረገውን የሚሊኒየም ግድብን በአምስት ዓመቱ ጊዜ ውስጥ ተግባራዊ እንዲሆን ሕብረተሰቡ የቦንድ ግዢ በመፈጸም ተሳትፎ እንዲያደርግ ቀስቅሰዋል፡፡
ኢህአዴግ እሁድ ዕለት ከአዲስ አበባ ከተማ ውጪ በክልል ዋና ዋና ከተሞች ላይም መሰል ሕዝባዊ ስብሰባዎችን ማድረጉን ምንጮቻችን ገልጸውልናል፡፡
በውይይቱ ላይ በደህንነት እና ጸጥታ ጉዳይ ላይ ንግግር ያደረጉት የኢህአዴግ አመራር አባላት ማንኛውም ሥራ መሥራትን የሚፈልግ ሰው በአነስተኛና ጥቃቅን ቢደራጅ ብድር ሊያገኝ እንደሚችልና በግሌ እሰራለሁ ብሎ የተነሳሳ ሰውም ቢሆን የቀበሌ መታወቂያ ያለው ዋስ እስከ አቀረበ ድርስ ብድር ሊያገኝ እንደሚችልና በሂደት ደግሞ የሥራው አዋጭነትና ግለሰቡ ብድሩን የመመለሱ ሁኔታ እየታየ የብድር መጠኑ ሊጨምርለት እንደሚችል ገልጸዋል፡፡