የአልጋን ቁርቋሬ ከሚያነጥፈው ይልቅ የሚተኛበት ያውቀዋል፡፡

‹‹አንድ ሺሕ ብር ብትጨምርም የመምህራን ችግር አይፈታም፤ ነጋዴውና ቤት አከራዩ ከጐን እየለበለበው ነው፤ የኑሮ ውድነቱ ችግር ደመወዝ በመጨመር አይፈታም፤ ያለው ችግር እንደ አገር መፍትሔ የሚያስፈልገው ነው::››  ይህ ከሰሞኑ የመምህራን የደመወዝ ጭማሪ በሚመለከት ከአንድ መምህር የተሰጠ አስተያየት ነው። በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ያለው ድባብ እጅግ በጠም አሳሳቢ እየሆነ ይገኛል።

በኢትዮጵያ ኑሮ በእጅጉ እየከበደ መሆኑን፣ መልካም አስተዳደር እየጠፋ ቢሮክራሲው በሙስና እየተጨማለቀና እየነቀዘ እንዳለ፣ ፍትሕ መደርመሱንና ገንዘብ በነጋሪት ጋዜጣ ላይ የበላይነት ማረጋገጡን የማያውቅ የለም፡፡ ሁሉም ያውቃል፡፡ ዕለታዊው የኅብረተሰቡ ወሬም ይህ ጉዳይ ሆኗል፡፡

መንግሥትም አያውቀውም አይባልም፤ ያውቃል፡፡ ቢሮክራሲውም በሌቦች የተሞላ መሆኑን፣ ሙስናና ኪራይ ሰብሳቢነት የልማት እንቅፋት መሆናቸውን፣ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የሕዝብ አመኔታ እያጡ በመምጣት ላይ መሆናቸውን፣ ወዘተ ራሱ መንግሥትም ይናገራል፡፡

ያም ሆነ ይህ በእርግጠኝነት መነገር ያለበት ቁምነገርና ሀቅ ግን አለ፡፡ እሱም ስለሚታየው የፍትሕ እጦት፣ ሙስና፣ አድልዎ፣ የገንዘብ የበላይነት፣ የቢሮክራሲው መዝቀጥ የተበዳይን ያህል የሚያውቅ አካል አለመኖሩን ነው፡፡ ተበዳይን ማዳመጥ ለመፍትሔው የጥበብ መጀመሪያ ነው፡፡

የአልጋን ቁርቋሬ ከሚያነጥፈው ይልቅ የሚተኛበት ያውቀዋልና፡፡
እስቲ ሁለት ማሳያዎችን እናንሳ

1.    ድህነት፣ ስደት፣ ውርደት፣ እስራት፣ ሞት

ሰሞኑን ዓለም ደቻሳ የተባለች ኢትዮጵያዊት የቤት ሠራተኛ በሊባኖስ ዋና ከተማ ቤይሩት ከተማ የደረሰባት ግፍና ሞት፣ ወደ ዓረብ አገሮች የሚደረገውን ስደትና የሥራ ፍለጋ ችግር እንድንመረምር ያስገድደናል፡፡ ቤይሩት በሚገኘው የኢትዮጵያ ቆንስላ በር ላይ በአሠሪዎቿ ስትደበደብ፣ በኃይል ተገዳና ታፍና መኪና ውስጥ ስትገባ የሊባኖስ መገናኛ ብዙኃን ይፋ አድርገውታል፡፡ በነጋታውም ይህች ታፍና መኪና ውስጥ እያለቀሰች የገባችው ኢትዮጵያዊት ‹‹ራስዋን ገደለች›› ተብሏል፡፡ እስካሁን ድረስ ቆንስላው በር ላይ ስትደበደብ ቆንስላው ለምን እንዳላስጣላትና ለምን ሁኔታውን ወዲያው ይፋ እንዳላደረገ የሚታወቅ ነገር የለም፡፡ ምንም እንኳን ዘግይቶ በጥቃት ፈጻሚው ላይ ክስ መመሥረቱ ተሰምቷል፡፡ የሊባኖስ መንግሥት ድርጊቱን ሲያወግዝና ይቅርታ ሲጠይቅ እንዲሁም በዳዩን ለሕግ እንደሚያቀርብ ሲናገር ተሰምቷል፡፡ ያም ሆነ ይህ ይቺ ምስኪን እንጀራ ፈላጊ እንደወጣች ቀርታለች፡፡

ላዩ ላዩ ሲታይና ሲነገር የሚሰማው በኩራት ይህን ያህል ሠራተኛ ወደ ውጭ አገር ሊላክ ነው ሲባል ነው፡፡ ዜጎች ከውጭ ገንዘብ ልከው ቤተሰቦቻቸውን ረዱ ሲባል ነው፡፡ ውስጡ ሲታይ ግን ከመንደር ጀምሮ እስከ ዓረብ አገር ድረስ ያለው ጉዞና ኑሮ በመከራና ስቃይ የተሞላ ነው፡፡ ኑሮ ሲከብዳቸው በደላላ ተገፋፍተው፣ ስማቸውን ቀይረው፣ በአዲስ አበባ በየጉራንጉሩ ለጤና በማይስማሙ ስርቻዎች ታሽገው፣ አላቅማቸው ለፓስፖርትና ቪዛ ከፍለው ይሄዳሉ፡፡ እዛያ ሲደርሱ ይዋረዳሉ፣ ይሰደባሉ፣ ይደበደባሉ፣ ያብዳሉ፣ ይታሰራሉ፣ ይሞታሉ፡፡ ዕደለኞች ከሆኑ ያለምንም ጥሪት ወደ አገር ቤት ይመለሳሉ፡፡ የአብዛኛዎቹ አስከሬን የትም ይጣላል፡፡ ውሻ ሲበላው የታየበት አጋጣሚ አለ፡፡

ዘርዝረን አንጨርሰውም እንጂ በየመን በኢትዮጵያውያን ላይ ለየት ያለው ግፍ እየተፈጸመ ነው፡፡ ስደተኛ ኢትዮጵያውያን ይያዛሉ፣ ይታገታሉ፡፡ አጋቾቹ ኢትዮጵያ ውስጥ ባሉ የእነሱ ደላሎች አማካይነት ከቤተሰቦቻቸው እስከ አራት ሺሕ አምስት መቶ ብር ይወስዳሉ፡፡ የከፈሉ አይነኩም፡፡ ያልከፈሉት ግን ለእስራትና ለሞት ይዳረጋሉ፡፡ የመን ያሉ አጋቾችና ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ደላሎች በጋራ የሚሠሩት ወንጀል ነው፡፡

ይህ አስከፊ ድርጊት ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያን ለውርደት እየዳረገ ነው፡፡ መሳቂያና መሳለቂያ እያደረገን ነው፡፡ መንግሥትም ሕዝብም ሊቃወሙትና ሊያወግዙት ይገባል፡፡ በስደት ላይ ሆነው በደል የደረሰባቸው መድረክ ይሰጣቸውና ይናገሩ፡፡ ዘመዶቻቸው ስቃያቸውን ይዘርዝሩ፡፡
የአልጋን ቁርቋሬ ከሚያነጥፈው ይልቅ የሚተኛበት ያውቀዋልና፡፡

2. የፍትሕ መደርመስ፣ የቢሮክራሲው መዝቀጥ፣ ንቅዘት በህዳሴ ላይ ብር በነጋሪት ጋዜጣ ላይ የበላይነት መረጋገጥ

ፍትሕን በማጠናከር፣ ቢሮክራሲውን በማጎልበት፣ የሕግ የበላይነት በማረጋገጥና ሙስናን በማጥፋት ህዳሴን እውን ለማድረግ መንግሥት አይፈልግም፤ ኢሕአዴግ አይፈልግም አንልም፡፡ ፍላጎቱ አለ፡፡ በተግባር ግን ፍላጎቱ የበላይነት ሊይዝ አልቻለም፡፡ ቀስ በቀስ ንቅዘት በህዳሴ ላይ የበላይነት እየያዘ ነው፡፡ ቀስ በቀስ ብር በነጋሪት ጋዜጣ ላይ የበላይነቱን እያረጋገጠ ነው፡፡ ቀስ በቀስ የፍትሕ አካል ተሰነጣጥቆ እየተደረመሰ ነው፡፡ ቢሮክራሲው ተጨማልቋል፡፡

ይህም ቢሆን ቁርቋሬውን የሚያውቀው ከአነጠፈው ይልቅ የተኛበት ነው፡፡
የሰነዶች ማስረጃና የሰው ምስክሮች በሚያስተማምን ሁኔታ በእጁ እያለ ሀቀኛ ባለጉዳይ የሚፈራበት ዘመን ላይ ነን፡፡ ምን ዋጋ አለው? ፍርድ ቤቱ በገንዘብ ቢገዛስ ብሎ ባለጉዳዩ ይሰጋል፡፡ ወንጀለኞች የበደሉ መሆናቸውን እየታወቀ ይስቃሉ፡፡ የፈለግነውን ከፍለን የፈለግነውን እናስወስናለን እያሉ ይፎክራሉ፡፡ በመጨረሻም ያሸንፋሉ፡፡ ገንዘብ ይስቃል፣ ይጮሃል፣ ይዘፍናል፣ ሕግና ፍትሕ ይሸማቀቃል፣ ይሳቀቃል፣ ያለቅሳል፡፡ ይህ በብዛትና በስፋት እየታየ ያለ መከራ ነው፡፡

ይህ አንቀጽ እንዲህ ይላል፣ ይህ ሕግ እንዲህ አስፍሯል ብሎ የሚናገር ሹመኛና ተንታኝ አልጠፋም፡፡ ለሕጉ ተግባራዊነት ዋጋ የሚከፍልና ለሀቅ ቆሞ ሕዝቡን የሚያገለግል ግን የለም፡፡ አንቀጾች ውበት እንጂ ተግባር መሆን አልቻሉም፡፡

በዚህ ብዙ ዜጎች እያለቀሱ ነው፡፡ ተስፋ እየቆረጡ ነው፡፡ ሀቅ ይዘው የሚደርስላቸው አጥተው እየተሰቃዩ ነው፡፡ አቤት የሚሉበት የለም፡፡

ወንጀለኛው ደግሞ ሲፈልግ ችሎት ያስቀይራል፤ ሲፈልግ የፖሊስ ምርመራ ያስቆማል፤ ሲፈልግ የታሰረ ያስፈታል፤ ሲፈልግ ንፁሀን ያሳስራል፤ ሲፈልግ እስረኛ ያስመልጣል፤ ሲፈልግ በቦሌ በኩል ለወንጀለኛ የአውሮፕላን ቲኬት ቆርጦ አሳፍሮ አሜሪካ ይልካል፤ ቤት ተከራይቶ ያኖራል፤ ከመንግሥት በላይ መንግሥት ይሆናል፡፡

የሚያሳዝነው የበደሉ ሰዎች ተገመገሙ ይባላል፡፡ ወንጀላቸው ተሸፍኖ በትምህርት ሰበብ ለቀዋል ይባላል፡፡ ሌላ ቤታ ሄደው ደግሞ ይሾማሉ፡፡ በተሾሙበት ሆነውም እንደገና ይፎክራሉ፡፡ ሀቀኛው ይፈራል፤ ወንጀለኛው ይፋፋል ያብጣል፡፡

የተበደለ፣ ጉቦ የተጠየቀ፣ ፕሮጀክቱ የተነጠቀ፣ ገንዘቡን የከሰረ እያለ ድምፁ የሚሰማውና ሰሚ የሚያገኘው የበደለውና የሰረቀው ነው፡፡

ይህ ሁኔታ በሀቀኞችና በኅብረተሰቡ ዘንድ ስጋት እየፈጠረ ነው፡፡ ሙስናን መዋጋት ያዋጣል ወይ? ሙሰኞች ተመልሰው እየተሾሙ እንዴት እንዋጋቸዋለን? እያለ እየፈራ ነው፡፡

መንግሥትም ሆነ ኢሕአዴግ እውነት ለመለወጥና ለመሻሻል ከፈለገ፤ ሙስናን ተዋግቶ ህዳሴን እውን ማድረግ ከፈለገ፣ የተበደለውን ኅብረተሰብ ማዳመጥ አለበት፡፡ በሩን ለባለገንዘብ፣ ለወንጀለኛና ለሙሰኛ ክፍት ማድረግ የለበትም፡፡

መንግሥት የመዋቅሩንና የቢሮክራሲውን ችግር አውቆ መፍትሔ መስጠት ከፈለገ፣ የሹመኞችን ተግባርና ማንነት አውቆ ትክክለኛ ዕርምጃ መውሰድ ከፈለገ ከተበደለው፣ ግፍ ከደረሰበት፣ አድልዎ ከተፈጸመበት ኅብረተሰብ ጋር መገናኘት አለበት፡፡ ማዳመጥ አለበት፡፡

የተበዳይ ጉዳይ በበዳይ አይጣራም አይወሰንም፡፡ ወንጀል የተፈጸመበት ዜጋ ጉዳዩ በወንጀለኛ አይጣራም፡፡ ድፍረት የሚጠይቅ የሕገ መንግሥትና የሕግ ጉዳይ በፈሪዎች አይጣራም አይወሰንም፡፡

መንግሥት ሀቀኛ ለውጥና ህዳሴ በማምጣት ሕዝባዊነቱን ማረጋገጥ ከፈለገ እየተበደለ ያለውን ሕዝብ በማነጋገር ያዳምጥ፡፡ ለመፍትሔ የሚሆን መረጃም፣ ማስረጃም፣ ሕዝባዊ ድጋፍም፣ ጉልበትም የሚያገኘው ያኔ ነው፡፡

የአልጋን ቁርቋሬ ከሚያነጥፈው ይልቅ የሚተኛበት ያውቀዋልና፡፡

2 thoughts on “የአልጋን ቁርቋሬ ከሚያነጥፈው ይልቅ የሚተኛበት ያውቀዋል፡፡

  1. Humni woyyaanee baqatee gara biyya ambaa adeemu fi humni hojii dhabee woyyaneef qaxaramee waraanu utuu wayyaanee itti galagalee lolee yaroo xinnoo keessatti woyyaanee fonqolcha ta’a.

Leave a comment