“የጋዜጠኝነት ሀሁ የማይገባቸው ጋጠወጦች” የወዲ ዜናዊ ሙያዊ አንደበት

(ቄሮ ዘጋቢ October 24, 2011) የወያኔ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው ማብራሪያ ከሰጡባቸው ጉዳዮች መካከል በፍርድ ቤት እየታየ ያለን ጉዳይ የሚዘግቡ ጋዜጠኞችን የሚመለከት ነው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዕለቱ ማብራሪያ  ሲሰጡ በቅርቡ ከሽብርተኝነት ጋር በተያያዘ የታሰሩ ሰዎችን በተመለከተ ነገሩ በፍርድ ቤት እየታየ ነው፡፡ በፍርድ ቤት እየታየ ያለን ጉዳይ የሚዘግቡ ጋዜጦች ክሱ ምን እንደሆነ ሳያዩ፣ ማስረጃዎችን ሳይመለከቱ ተጠርጣሪዎቹ ነፃ ናቸው የሚሉት የፍርድ ሒደቱ በፍጥነት ባለመከናወኑ ሳይሆን፣ የጋዜጠኝነት ሀሁ የማይገባቸው ወይም እንዲገባቸው የማይፈልጉ ጋጠ ወጦች በመሆናቸው ነው፡፡

ጋዜጦችን ክሱ ምን እንደሆነ ሳያዩ፣ ማስረጃዎችን ሳይመለከቱ ተጠርጣሪዎቹ ነፃ ናቸው የሚሉት የፍርድ ሒደቱ በፍጥነት ባለመከናወኑ ሳይሆን፣ የጋዜጠኝነት ሀሁ የማይገባቸው ወይም እንዲገባቸው የማይፈልጉ ጋጠ ወጦች በመሆናቸው ነው፡፡

ወዲ ዜናዊ  በመቀጠልም የጋዜጠኛ የመጀመሪያ ሥነ ምግባር የሁለቱን አስተያየት መስማት ነው፡፡ ነገሮችን በጥሞና ማጥናት ነው፡፡ ማስረጃዎችን መፈተሽ ነው፡፡ ይህን ሳያደርጉ ዘሎ አለመጻፍ አለመናገር ነው፡፡ የጋዜጠኝነት ሥነ ምግባር የሚጠይቀው ይኼን ነው፡፡ ይኼን ሥነ ምግባር አልፈው የሚንጣጡ ጋዜጠኞች ካሉ ችግሩ የራሳቸው እንጂ ለፍርድ ቤት በማቅረብ ላይ መዘግየት ስለታየ አይደለም፡፡

በአሁኑ ሰዓት በአገራችን የሚካሄደው የሽብር እንቅስቃሴ ሦስት ዋና ዋና ተዋናዮች አሉት፡፡ አንደኛውና ዋናው የኤርትራ መንግሥት ነው፡፡ የእዚህን ቡድን አቋም ሕዝቡ ያውቀዋል፡፡ ሻዕቢያ የአቋም ለውጥ አላሳየም፡፡ አካባቢውን የማተራመስ ስትራቴጂ ይዞ ነው እየሠራ ያለው፡፡ ሁለተኞቹ ሻዕቢያ በቀጥታ የሚያሰማራቸው ነጭ ለባሾች ናቸው፡፡ እነዚህ አልሻባብን ይመለከታሉ፡፡ ኦነግን፣ ኦብነግንና ግንቦት 7 ብሎ የሰየመውን ቡድን ይመለከታሉ፡፡ እነዚህ ቡድኖች በዚህ ፓርላማ አሸባሪ ተብለው ተፈርጀዋል፡፡ ዋና ቢሮአቸውም አስመራ ነው፡፡ የሚንቀሳቀሱትም አስመራ በተቀየሰው ስትራቴጂ መሠረት ነው፡፡ እነዚህ በጣም የታወቁ ተዋንያን ናቸው፡፡ ቀሪዎቹ ደግሞ በሰላማዊ መንገድ እንሠራለን ብለው ያወጁ ናቸው፡፡ አንዳንድ የመድረክ መሪዎች ከእነዚህ የሻዕቢያ ነጭ ለባሾች ጋር በመተባበር በሕጋዊ ፓርቲ ሽፋን የነኦብነግ፣ የነኦነግና የግንቦት 7 አስፈጻሚ ሆነው እየሠሩ ነው፡፡ አሁን የታሰሩ ሰዎች አሉ፡፡ እነዚህ የታሠሩት ሰዎች የአሸባሪ ድርጅት አባላት መሆናቸውን የሚያሳይ አሳማኝ ማስረጃ አለን፡፡

ማን የማን ድርጅት አባል መሆኑን እያወቅን ያላሰርናቸው ሰዎች አሉ፡፡ እነዚህን ግለሰቦች ያላሰርንበት ምክንያቱ ሁለት ነው፡፡ የመጀመሪያው ሰዶ ማሳደድ አያስፈልግም በሚል ነው፡፡ በፍርድ ቤት ተቀባይነት ያለው ማስረጃ ስላላገኘንባቸው ዝም ያልናቸው አሉ፡፡ እስካሁን ለታሰሩት ግን የአሸባሪ አባል ስለመሆናቸው አሳማኝ ማስረጃ አለን፡፡

ብዙዎቹ እነዚህ ሰዎች በምህረት የተለቀቁ ናቸው፡፡ በቅድመ ሁኔታ ነው የተፈቱት፡፡ ዝም ብለን ማሰር ብንፈልግ እያንዳንዳቸው የገቡትን ቃል በየቀኑ ያፈረሱበት ሁኔታ ስላለ ሁሉንም ጥፍር አድርገን ማስገባት እንችላለን፡፡ በየጋዜጣው መአት ማስረጃ አለ፡፡ በቀጥታ ወደ ይቅርታ ቦርድ ተወስደው [የገቡትን ቃል] ጥሰዋል አልጣሱም በሚል እስር ቤት ማስገባት እንችላለን፡፡ ይህንን ያላደረግንበት ምክንያት በሒደት እየረገቡ እየገባቸው ይሄዳል፤ ከግለሰቦች ጋር አተካራ መግባት አይገባንም በሚል ነው፡፡ እነዚህ ድርጅቶች ውስጥ ያሉ አመራሮች ማ የየትኛው አሸባሪ ድርጅት አባል እንደሆነ በዝርዝር ነው የምናውቀው፡፡ በምናውቀው ልክ ዕርምጃ አልወሰድንም፡፡

አንዳንድ ጋዜጠኞች ከየትኛው የአሸባሪ ድርጅት ጋር እንደሚገናኙና ምን ዓይነት መመርያ እንደሚሰጣቸው እናውቃለን፡፡ ምኅዳር ለማጥበብ የሚባለው የቁራ ጩኸት ነው፡፡ በዚህ ሥራ የተሰማሩ ሰዎችን ማሰር ከፈለግን ከመጠን በላይ ማስረጃ አለን፡፡ ስለታገስን የማናውቅ ከመሰላቸው እየተሳሳቱ ነው፡፡ መንግሥት አሳማኝ ማስረጃ ሳይዝ አይገባም፡፡ የሚሠሩት ድራማ በዝርዝር መታወቁ አይቀርም፡፡

Leave a comment