(ቄሮ ዘጋቢ October 24, 2011)በደቡብ ክልል ሃዲያ ዞን የምሥራቅ ባዳዋቾ የፖሊስ አባላት ባደረሱት ጥቃት ሦስት ሰዎች ሲገደሉ፣ በ27 ሰዎች ላይ ቀላልና ከባድ ጉዳት መድረሱንና 115 ቤቶች በውስጣው ከነበሩ የቤት እንስሳትና ንብረቶች ጋራ መቃጠላቸውን ተዘገበ፡፡
ላለፉት 13 ዓመታት “እኛ ሃላባዎች እንጂ ሃድያዎች አይደለንም፤” በሚል የማንነት ጥያቄ ሲያነሱ የቆዩት በሃዲያ ዞን ውስጥ የሚገኙ ሦስት ወረዳዎች፣ ጥያቄያቸው ምላሽ በማጣቱ ወደ ግጭት በማምራት ላይ መሆናቸውን ተገልጸዋል፡፡
ቁጥራቸው አሥር የሚደርሱ በሃዲያ ዞን ምሥራቅ ባዳዋቾ ወረዳ የአንደኛ ቄራንሶ፣ የሁለተኛ ቄራንሶና የገገራ ቀበሌ ነዋሪዎች ተወካይ ሽማግሌዎች እንደገለጹት፣ ለ13 ዓመታት የማንነት ጥይቄያቸውን ለወረዳው፣ ለዞኑ እንዲሁም ለደቡብ ክልል ከዚያም አልፎ ተርፎ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ቢያቀርቡም ምላሽ ከማጣታቸውም ባሻገር ወደ ግጭት እያመሩ ነው፡፡
ባህላቸው፣ ታሪካቸውና ቋንቋቸው የሃላባ መሆኑን የሚናገሩት እነዚሁ ሽማግሌዎች፣ “እውነታው ይህ ሆኖ እያለ የምንማረው፣ የምንዳኘው እንዲሁም ማንኛውንም ማኀበራዊና ፖለቲካዊ ግንኙነታችንን የምናደርገው በምንም መልኩ መናገር፣ መስማትና ማንበብ በማንችለው የሃዲይኛ ቋንቋ ነው፤” በማለት ይገልጻሉ፡፡
በ1989 ዓ.ም. ብሔረሰቡ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት አቤቱታውን ባሰማበት ወቅት፣ ምክር ቤቱ ለደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልላዊ መንግሥት ምክር ቤት በጻፈው ደብዳቤ፣ የክልሉ ሕገ መንግሥት በሚፈቅደው መሠረት ጥያቄው በክልሉ በኩል ተጣርቶ ውሳኔ እንዲያገኝ አዟል፡፡
የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል መንግሥት የብሔረሰቦች ምክር ቤት ጽሕፈት ቤትም፣ በ1998 ዓ.ም. ለጉራጌ፣ ለስልጤ፣ ለሃዲያና ለከንባታ ዞኖች አስተዳደር ጽሕፈት ቤቶችና ለሃላባ ልዩ ወረዳ አስተዳደር ጽሕፈት ቤት የላከው ደብዳቤ፣ የማንነት ጥያቄ የሚያነሱትን ብሔረሰብ አባላት ጥያቄ አጣርተው መፍትሔ እንዲያገኙ ያዛል፡፡
“ከሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት በተደጋጋሚ ትዕዛዝ ይምጣ እንጂ ለጥያቄያችን ምላሽ ከማግኘት ይልቅ ስቃይና እንግልት እየበዛብን መጥቷል፤” የሚሉት ተወካዮቹ፣ እየደረሰባቸው ስላለው የሰብዓዊ መብት ረገጣም ለሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የድረሱልን ጥሪ ማቅረባቸውን ገልጸዋል፡፡
ጥር 20 ቀን 2000 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ለክልሉ መንግሥት የላከው ደብዳቤ እንደሚያመለክተው፣ የሦስቱ ቀበሌ ነዋሪዎች በሃዲያ ዞን የምሥራቅ ወረዳ አመራር አባላት ለጥያቄያቸው ምላሽ ከመስጠት ይልቅ በተወካዮቻቸው ላይ ድብደባና አፈና እያደረሱባቸው መሆኑን፣ ከዚህም ለማምለጥ አካባቢውን ለቅቀው በስደት እንደሚገኙና የማንነት ጥያቄውን ባቀረቡ ተወካዮች ቤተሰቦች ላይ እስራት እንደሚፈጸምባቸው ተወካዮቹ በአቤቱታቸው ማቅረባቸውን ይገልጻል፡፡ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በብሔሩ ላይ እየደረሰ ያለውን የመብት ጥሰት እንዲያስቆምላቸውና በሃላባ ብሔረሰብ ውስጥ መከለል የሚችሉበትን ሁኔታ እንዲያመቻችላቸው የጠየቁ መሆናቸውንም ያመለክታል፡፡
ኮሚሽኑ የብሔሩን አቤቱታ መሠረት በማድረግ ለክለሉ በጻፈው ደብዳቤ፣ በሰዎቹ ላይ የአካባቢው የአስተዳደር አባላት እያደረሱ ያሉትን በደል ክልሉ እንዲያስቆምላቸውና ለዘለቄታውም በፌዴራልና በሕገ መንግሥት የተቀመጡትን አቅጣጫዎች በመከተል የአከላለል ጥያቄያቸውን እንዲፈታላቸው ያሳስባል፡፡
የማንነት ጥያቄ መነሳት ከጀመረበት ከ13 ዓመታት ወዲህ በብሔረሰቡ ላይ እየደረሰ ያለው ስቃይ ከልክ በላይ መሆኑን የሚናገሩት ተወካዮቹ፣ ዞኑ ለችግሩ መፍትሔ ከማቅረብ ይልቅ ቅድመ ሁኔታዎችን በመደርደር እየበደላቸው መሆኑን ይገልጻሉ፡፡
“ከፈለጋችሁ መሬቱ የሃዲያ ስለሆነ ለቃችሁ ሂዱ፣ ካልሆነም ሃዲያ ባትሆኑም ሃዲያ ነን በሚል አማራጭ ኑሩ፤” የሚሉ ሁለት አማራጮች እንደቀረቡላቸው ገልጸዋል፡፡
የማንነት ጥያቄ የሚያነሱትን በጅምላ በማሰር፣ በመደብደብና ባልሠሩት ወንጀል በማስፈረድ ተደጋጋሚ እንግልት እንደሚያደርሱባቸው የሚናገሩት ተወካዮቹ፣ በተለይ መስከረም 21 ቀን 2000 ዓ.ም. “ሕገወጥ ስብሰባ አካሂዳችኋል፤” በሚል ወረዳው ባሰማራቸው የፖሊስ ኃይል የደረሰው ጥቃት ችግሩን አስከፊ እንዳደረገው አብራርተዋል፡፡ በዚሁ ዕለት የምሥራቅ ባዳዋቾ የፖሊስ አባላት ባደረሱት ጥቃት ሦስት ሰዎች ሲገደሉ፣ በ27 ሰዎች ላይ ቀላልና ከባድ ጉዳት መድረሱንና 115 ቤቶች በውስጣው ከነበሩ የቤት እንስሳትና ንብረቶች ጋራ መቃጠላቸውን ተወካዮቹ ገልጸዋል፡፡
ጥቃቱን ካደረሱ በኋላም ሕፃናትና አዛውንትን በማሰር ላይ በመሆናቸው በአሁኑ ወቅት አብዛኛው ሕዝብ በፍርኃት በጫካ ውስጥ ተሸሽጐ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡ ጉዳዩን አስመልክተን ማብራሪያ እንዲሰጡን የጠየቅናቸው የምሥራቅ ባዳዎቾ አስተዳደር ኃላፊ፣ “ሃላባና ሃዲያ የሚባል ነገር የለም፡፡ ግጭቱም የሃላባና የሃዲያ ሳይሆን የግለሰቦች ግጭት ነው፡፡ ከዚህ በላይ ማብራሪያ መስጠት አልፈልግም፤” በማለት መልሰውልናል፡፡
በአካባቢው የተነሳውን ግጭት ለማብረድ የደቡብ ክልል የፖሊስ ኃይል ወደ አካባቢው ገብቶ ሁኔታውን በማረጋጋት ላይ መሆኑን ከክልሉ ያገኘነው መረጃ ያመለከታል፡፡ በሦስቱም ቀበሌዎች ቁጥራቸው ከ25 ሺሕ በላይ የሆኑ የሃላብኛ ቋንቋ ተናጋሪ ነዋሪዎች እንደሚኖሩ ለማወቅ ተችሏል፡፡
source: http://www.ethiopianreporter.com/news/293-news/3850—13——-.html