(የቄሮ ዜና ምንጭ /ቄዜም/ ፍንፍኔ ሀምሌ 12፣2011) የዘረኛው መለስ ዜናዊ አገዛዝ በታሰሩ የኦሮሞ እና ሌሎች የፖለቲካ እስረኞች ላይ የሚፈጸመው ሰቆቃ የሚያጋልጥ ባለ 24 ገጽ ሪፖርት ለተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብት ኮሚቴ መቅረቡ ተዘገበ።
የአለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተከራካሪ ድርጅት አምንስቲ ኢንተርናሽናል እንደፈረንጆች አቆጣጠር ጁላይ 11 ቀን በጄነቫ ሲውዘርላንድ ለተሰየመው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብአዊ መብት ኮሚቴ እንዳጋጠው ፤ የመለስ ዜናዊ አገዛዝ በታሰሩ እስረኞች ላይ የፈጸማቸው ዘግኛኝ ሰቆቃዎች እንዲመረምሩና ለድርጊቱ ተጠያቂ የሆኑ አካላት ለፍርድ እንዲቀርቡ ጠይቋል።
በኦሮሞ እና በግንቦት 7 የፖለቲካ እስረኞች ላይ የተፈጸመውን አሰቃቂ የግርፋት አይነቶች የዘረዘረው የአምንስቲ ኢንተርናሽናል ሪፖርት በተለይ በኦነግ ደጋፊነት ተጠርጥረው በገፍ በሚታሰሩ የኦሮሞ ተወላጆች ላይ ተመሳሳይ የሆነ ስብዕናን የሚነካና የሚዘገንን ጥቃትና ሰቆቃ መፈጸሙን እንዳረጋገጠ አጋልጧል።
በሺዎች የሚቆጠሩ የኦሮሞ ተወላጆች ኦነግን ትደግፋላችሁ በሚል ሰበብ ብቻ በኦሮሚያ ክልል በሚገኙ ፖሊስ ጣቢያዎች ፤ ወህኒ ቤቶች፤ ወታደራዊ ማሰልጠኛ ካምፖች እና ድብቅ በሆኑ ማጎሪያ ቤቶች እየታሠሩ አሰቃቂ የሆነ ድብደባ ይፈጸምባቸዋል ያለው አምንስቲ፤ ታሳሪዎች ገላቸውን በአለንጋ ይተለተላሉ ፤ ይረገጣሉ፤ በጋለ ብረት ይተኮሳሉ ፤ ሴቶች ተገደው ይደፈራሉ፤ ብልታቸው ውስጥ ጠርሙስ እና ሌላ አሰቃቂ ቁስ በመክተት ለስቃይ ይዳረጋሉ በማለት ከከሰሰ በኋላ ይህ ሁሉ ስቃይ የተፈጸመባቸው እስረኞች ያለፍርድ ለረጅም ጊዜ እሥር ቤት ይሰቃያሉ ሲል ሪፖርቱ ይገልጻል።
ሃረር ውስጥ በንግድ ሥራ ይተዳደሩ በነበሩት በአቶ ሙላቱ አበራ ላይ የተፈጸመው ጭካኔ የተሞላበት ሰቆቃ በብዙ የኦነግ ተጠርጣሪ እስረኞች ላይ እንደሚፈጸም ግልጽ ነው ያለው አምኒስቲ ለ3ኛ ጊዜ በኦነግ ደጋፊነት ተጠርጥሮ ወደ ሃረር ማዕከላዊ ፖሊስ የተወሰደው አቶ ሙላቱ ፤ የጎን ስፋቱ 4 ሜትር ቁመቱ አንድ ሜትር በሆነ ከምድር በታች ባለ አንድ ጠባብ የጨለማ ክፍል ውስጥ ከሌሎች 3 ታሳሪዎች ጋር እርቃኑን እንዲታሰር ከተደረገ በኋላ ማታ ማታ ቀዝቃዛ ውሃ ከአናታቸው ላይ እየተንጠባጠበ እንዲሰቃዩ መደረጋቸውንም አጋልጦአል።
እነ አቶ ሙላቱ የታሰሩበት ክፍል ውስጥ እስረኞች እንዳይተኙ በሚል ሹል ሆኖ የተጠረበ ድንጋይ እንደተነጠፈበት፤ ሲደክማቸው ግድግዳውን ተደግፈው እንኳን እንዳይቆሙ የክፍሉ ጣሪያ ከፍታ አንድ ሜትር ብቻ እንደሆነና፤ በዚህ ላይ ወገባቸው ላይ የብረት ካቴና ከታሰረ በኋላ ህመም እንዲሰማቸው በየቀኑ ብሎኑ እንዲጠብቅ ይደረጋል ሲል ዘግቧል። በዚህም የተነሳ የአቶ ሙላቱ የወገብ አጥንት ለስብራት በቅቶአል በማለት በዜጎቻችን ላይ እየደረሰ ያለውን ስቃይ ሪፖርቱ ይፋ አድርጎል።
የወንድ ብልታቸው ላይ በገመድ ጠርሙስ እንዲንጠለጠል በማድረግ በህመም ስቃይ ውስጥ ሆነው ያልሰሩትንና የማያውቁትን ወንጀል ጭምር እንዲናዘዙ ይደረጋሉ ያለው አምኒስቲ ከግንቦት 7 ጋር የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ሊያደርጉ ነው ተብለው በማዕከላዊ ወንጀል ምርመራ ዘግናኝ የሆነ ድብደባ ከተፈጸመባቸው መሃል አቶ ጌቱ ወርቁና ጀኔራል አሳመነው ፅጌ ገለልተኛ በሆነ ሃኪም እንዲታዩና የህግ ጥበቃ እንዲደረግላቸው ለፍርድ ቤት አቤቱታ አቅርበው ተቀባይነት አለማግኘታቸው ይታወሳል።
አምኒስቲ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብአዊ መብት ኮሚቴ ባቀረበው በዚህ ሪፖርቱ በኢትዮጵያ እስር ቤት ውስጥ ባሉት እሰረኞች ላይ የተፈጸመውን ጭካኔ የተሞላበት ሰቆቃ በገለልተኛ አካል እንዲመረመርና ሰቆቃ ፈጻሚዎቹ በአስቸኳይ ህግ ፊት እንዲቀርቡ ተማጽኖአል።
