የኢትዮጵያ መንግስት በኦሮምያ እያካሄደ ያለዉ የጦር ወንጀል (War Crime) በሁሉም የዓለም ማህበረ-ሰብ ልወገዝ ይገባል!

ከኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ከፍተኛ ወታደራዊ አመራር የተሰጠ መግለጫ

(ኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ከፍተኛ ወታደራዊ አመራር,ግንቦት 24 , 2011 ዓም) ካለፈዉ ጥር 2011 ዓም አጋማሽ ጀምሮ ለስሙ “የሀገር መከላከያ ሠራዊት” በሚል ስያሜ የሚታወቀዉ የኢሕአዴግ ጦር በኦሮሞ ሕዝብና በኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ላይ የሚያካሄደዉን ጦርነት ወደ አየር ድብደባ ማሳደጉ የሚታወስ ነው። በዚህም መሠረት ጥር 4 እና 5 2011 ዓም በምዕራብ ኦሮምያ በቄለም ወለጋ ዞን በጊዳሚ ወረዳ ዉስጥ ጃል መሮ (ኩምሣ ዲሪባ)ን ለመግደል ታቅዶ የተሰነዘረዉን የአየር ድብደባ በማካሄድ በሰላማዊ (ትጥቅ-ኣልባ) ዜጎች ህይወትና ንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱ በወቅቱ ተዘግቦ ነበር። በዚያ ጥቃት ዒላማዉን እንደሳተ ስረዳዉ ግን “የአየር ድብደባዉን ኣላካሄድኩም” ስል ኣይኑን በጨዉ ኣጥቦ ለመካድ ሞከረ።

ካለፉት ሁለት ወራት ወዲህ ደግሞ እጅግ ዘግናኝና ኣሳዛኝ በሆነ መልኩ ከፍተኛ የጦር ወንጀሎችን በኦሮሞ ሕዝብ ላይ እያካሄደ ይገኛል። ይህንንም እያደረገ ያለዉ የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ይግኝባቸዋል ተብሎ በሚታሰቡና ሰላማዊ ሕዝብም በሚኖርባቸዉ የምዕራብ ኦሮምያ ደኖች ላይ የጦር ሄሊኮፕቴሮችን ተጠቅሞ በዓለም-ኣቀፍ ህግ የተከለከለዉን መርዛማ ጋዝ በመርጨት ጭምር ነው። በነዚህ ዘግናኝና ኣሳፋሪ ጥቃቶች እስካሁን የበርካታ የዱርና የቤት እንስሳት ህይወት የጠፋ ስሆን በኣንዳንድ ቦታዎች ደግሞ የተወሰኑ ሰዎች ላይ ያልተለመዱ ዓይነት የጤና እክሎች ታይቷል።

ለ27 ዓመታት በስመ-ዴሞክራሲ የሀገሪቱን ሕዝቦች በጠብ-መንጃ ኣፈሙዝ ኣገዛዝ ሥር ስያንገላታ ከነበረዉ ከኢህአዴግ ዉስጥ በተሃድሶና በለዉጥ ኣራማጅነት ስም ወደ ስልጣን የመጣዉ የዶ/ር አብይ አህመድ አስተዳደር ስርዓቱን ወደ ዴሞክራሲ ለማሻገር የገባዉን ቃል በማጠፍ ይህንን እጅግ ከፍተኛ የሆነ ወንጀል መፈጸሙ በእጅጉ ኣስደንጋጭ፣ ኣሳዛኝና ኣስነዋሪም ነዉ። በዶክተር አብይ አህመድ አስተዳደር ሆን ተብሎ በኦሮሞ ሕዝብ ላይ እየተካሄደ ያለዉ ይህ ከፍተኛ የጦር ወንጀል (War Crime) በዓለም-ኣቀፉ ማህበረ-ሰብ ዘንድ ታዉቆ መወገዝና በኣስቸኳይ እንድገታም መደረግ ይኖርበታል። ይህ ካልሆነ ከዚህ ጋር ተያይዞ ለሚመጣዉ ኣደጋ ሁሉ የመጀመሪያዉ ተጠያቂ ዶክተር አብይ አህመድ እና አስተዳደራቸዉ፣ እንድሁም ድርጅታቸዉ ኦዴፓ/ኢህአዴግ መሆኑን በጥብቅ እናሳስባለን።

ለፍትህ፣ ለሕዝቦች ነፃነት፣ እንድሁም ለእዉነተኛ ዴሞክራሲ የሚቆሙና ሰላም ወዳድ የሆኑ የዓለም ማህበረ-ሰብ እና መንግስታት ሁሉ፣ የዜና አዉታሮች፣ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች … ወዘተ በተቻላቸዉ መንገድ ሁሉ የራሳቸዉን ክትትልና ጥናት በማካሄድ ስለዚህ ዘግናኝ እዉነታ በራሳቸዉ መንገድ እንድያረጋግጡም ጥሪ እናቀርባለን።

በመጨረሻም፣ ሕዝባችን ከምስራቅ እስከ ምዕራብ፣ ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ እንድሁም ከሀገር ዉስጥና ከዉጭ እጅ-ለእጅ ተያይዞ ይህንን ዘግናኝ ግፍ ለማስቆም እንድረባረብ የትግል ጥሪያችንን እናቀርባለን። በኣፍ ብቻ እራሱን የለዉጥ ኣራማጅና መሪ ኣድርጎ ከመመጻደቅ ኣልፎ አስተዳደሩ በኦሮሞ ሕዝብ ዘንድ “የኦሮሞ መንግስት” እንድባልለት ሕዝባችንን እያወናበደ፣ በተግባሩ ግን ክእሱ በፊት የነበሩት መሪዎች እንኳን ያልፈጸሙትን ዘግናኝ ግፍና ወንጀል በሕዝባችን ላይ እየፈጸመ ባለዉ የዶክተር አብይ አስተዳደር ላይ ኣስፈላጊዉን ጫና ሁሉ በማሳረፍ ከተያያዘዉ የጥፋት ጎዳና እንድመለስ ማድረግ እና ካልተመለሰ ደግሞ በትግል ማስወገድ ታሪካዊ ግዴታ ነዉ ብለን እናምናለን። በዚህ ሂደትም ቄሮ (Qeerroo) ከሁሉም የላቀ ድርሻዉን እንደሚወጣ ኣንጠራጠርም !

ድል ለኦሮሞ ሕዝብ !

የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ከፍተኛ ወታደራዊ አመራር

ግንቦት 24 , 2011 ዓም

 

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s