የእንጦጦ ቱሪስት ማዕከል ግንባታ ጨረታ ሊወጣ ነው:የዳግማዊ ምኒልክና የአፄ ቴዎድሮስ አደባባይ ሊታደሱ ነው::

የእንጦጦ ቱሪስት ማዕከል ግንባታ ጨረታ ሊወጣ ነው:ፕሮጀክቱ 4.8 ቢሊዮን ብር እንደሚፈጅ ተገምቷል
የዳግማዊ ምኒልክና የአፄ ቴዎድሮስ አደባባይ ሊታደሱ ነው

 

  • ፕሮጀክቱ 4.8 ቢሊዮን ብር እንደሚፈጅ ተገምቷል
  • የዳግማዊ ምኒልክና የአፄ ቴዎድሮስ አደባባይ ሊታደሱ ነው

(Ethiopian Reporter) –አዲስ አበባን የቱሪስት ማዕከል ያደርጋታል የተባለው ግዙፍ የሆነው የእንጦጦ ቱሪስት መዳረሻ የንድፍና የግንባታ ሥራ ጨረታ ሊወጣ ነው፡፡

የአዲስ አበባ ከተማን በዓለም አቀፍ የቱሪስት መዳረሻ ካርታ ውስጥ እቱሪስትንደሚያስገባ የታመነበት በሰሜን አዲስ አበባ በእንጦጦ ጥብቅ ደን ከየካ ዋሻ ሚካኤል እስከ ጉለሌ የዕፅዋት ማዕከል በተንሰራፋ 4,200 ሔክታር ተራራማ ቦታ ላይ፣ በ4.8 ቢሊዮን ብር ወጪ በርካታ የመዝናኛ ማዕከላትና የቱሪስት አገልግሎት መስጫ ተቋማት ለመገንባት ታቅዷል፡፡

የቱሪስት ማዕከሉ በዋናነት የመዝናኛ፣ የዕደ ጥበብ መሥሪያ፣ የመሸጫና ማሠልጠኛ፣ የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የባህል ማዕከልና ዓለም አቀፍ የአትሌቲክስ መንደር ግንባታን አቅፎ የያዘ ነው፡፡

ማክሰኞ ሰኔ 13 ቀን 2009 ዓ.ም. በጌትፋም ሆቴል በተካሄደው የአዲስ አበባ ከተማ ቱሪዝም ትራንስፎርሜሽን ምክር ቤት ሦስተኛ ዓመታዊ ጉባዔ ላይ ማብራሪያ የሰጡት የእንጦጦና አካባቢዋ የቱሪስት መዳረሻ ልማት ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ህያብ ገብረ አምላክ፣ የፕሮጀክት ትግበራ ቅድመ ዝግጅት ሥራዎች በመካሄድ ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ የአዋጭነት ጥናት መካሄዱን፣ የንድፍና ግንባታ ሥራ ጨረታ ለማውጣት የጨረታ መሥፈርቶችን ዝግጅት ባለፈው ሳምንት መጠናቀቁን ተናግረዋል፡፡ የንድፍና የግንባታ ጨረታ በአንድነት ወይም በተናጠል ሊወጣ እንደሚችል የጠቆሙት ዶ/ር ህያብ ሁለቱም አማራጮች ያላቸው ጠቀሜታና ጉድለት ተሠርቶ ለአመራሩ ለውሳኔ እንደሚቀርብ ተናግረዋል፡፡

አመራሩ በሚሰጠው ውሳኔ መሠረት ጨረታውን በሐምሌ ወር ለማውጣት፣ የፕሮጀክቱን ግንባታ በጥር ወይም የካቲት ወር 2010 ዓ.ም. ለመጀመር መታቀዱን ተናግረዋል፡፡

የእንጦጦና አካባቢዋ የቱሪስት መዳረሻ ልማት ፕሮጀክት ከሚገነባበት 4,200 ሔክታር መሬት 60 በመቶ ወይም 2,500 ሔክታር መሬት የተራቆተ በመሆኑ፣ ሁለት ሚሊዮን ዛፎች በመትከል ሰፊ የደን ማልበስ ሥራ እንደሚሠራ ተገልጿል፡፡ የአዲስ አበባ ነዋሪዎችና ቱሪስቶች ራሳቸውን የሚያድሱባቸው ሰፊ መናፈሻዎች፣ የመዋኛ ገንዳዎች፣ አዕዋፍትን የሚስቡ ኩሬዎች፣ የሕፃናት መጫወቻ ሥፍራዎች፣ የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎች፣ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የአትሌቲክስ መንደር፣ ሎጆች፣ የዱር እንስሳት ፓርኮች፣ የፈረስ መጋለቢያ ሥፍራ፣ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች የቤት ግንባታ፣ ባህልና አኗኗር የሚያሳይ የባህል ማዕከል፣ የዕደ ጥበብ ማምረቻ፣ መሸጫና ማሠልጠኛ ተቋምና የሙዚየሞች ግንባታ በፕሮጀክቱ ተካተዋል፡፡

ከሁሉም በላይ የአዲስ አበባ ከተማ ልዩ መለያ የሚሆን 500 ሜትር ርዝመት ያለው ማማ ለመገንባት መታቀዱን ተናግረዋል፡፡ የማማው አናት በኦዳ ቅርፅ የሚሠራ ሲሆን የፋሲል ግንብ፣ የአክሱም፣ የላሊበላና የሐረር ግንብ በሥነ ሕንፃዎች እንደሚካተቱ ተገልጿል፡፡ ማማው የአዲስ አበባ ዙሪያ ገባ መመልከቻ ክፍሎች፣ የምግብ ቤቶችና የተለያዩ ሙዚየሞች ይኖሩታል፡፡

የእንጦጦ የቱሪስት መዳረሻ 14,000 የሥራ ዕድል እንደሚፈጥር ቱሪስት ከመሳብ ባሻገር በርካታ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጠቀሜታ እንደሚኖረው ዶ/ር ህያብ አስረድተዋል፡፡ ‹‹ለሥራ ዕድል ፈጠራ፣ ለገጽታ ግንባታና ግንባታው የደን ሀብቱን ሳይነካ ኤኮ ቱሪዝምን የሚያስፋፋ በመሆኑ በአካባቢ ጥበቃም ትልቅ ጠቀሜታ ይኖረዋል፤›› ያሉት ዶ/ር ህያብ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከፍተኛ አመራር በፕሮጀክቱ ሒደት ላይ የቅርብ ክትትል በማድረግ ላይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ስብሰባውን የመሩት የአዲስ አበባ ከንቲባና የአዲስ አበባ የቱሪዝም ትራንስፎርሜሽን ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ድሪባ ኩማ፣ የፕሮጀክቱ አዋጭነት ጥናት በዓለም ባንክ ተጠንቶ አዋጭ መሆኑ እንደተመለከተ አስረድተዋል፡፡ ፕሮጀክቱ ግዙፍና ለመጪዎቹ ትውልዶች የሚተላለፍ በመሆኑ፣ እንዲሁም በጥብቅ ደን ውስጥ የሚካሄድ ስለሆነ ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚጠይቅ እንደሆነ የተናገሩት አቶ ድሪባ፣ ከምሁራንና ከከተማዋ ነዋሪዎች ጋር ውይይት እንደሚካሄድ ገልጸዋል፡፡

ተራራማና በደን የተሸፈኑ ቦታዎችን አካባቢ ሳያዛቡ ተመሳሳይ የቱሪስት ማዕከላትን ከገነቡ ቻይና፣ ኮሪያና ፈረንሣይ ልምድ መቀሰሙን የገለጹት አቶ ድሪባ የታሪክ ምሁራን፣ የሥነ ሕንፃ ባለሙያዎች፣ በሆቴልና ቱሪዝም ሥራ ከተሰማሩ ዜጎች ጋር ምክክር እንደሚደረግና ከከተማዋ ነዋሪዎች ጋር ውይይት በማካሄድ ጠቃሚ ሐሳቦች ተሰብስበው የፕሮጀክቱ ዕቅድ ውስጥ እንደሚካተቱ ተናግረዋል፡፡

ተመሳሳይ ፕሮጀክቶችን ያለሙ አገሮች ባለሙያዎች ሐሳብ በግብዓትነት ለመውሰድ መታሰቡንና የፌዴራል መንግሥት አስተያየትና ዕገዛ እንደሚታከልበት ከንቲባው ጠቁመዋል፡፡

በእንጦጦ የቱሪስት መዳረሻ ልማት ፕሮጀክት የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ ምን መልክ እንደሚኖረው ከሪፖርተር ለቀረበላቸው ጥያቄ አቶ ድሪባ ሲመልሱ፣ መንግሥት የሚገነባው ዋና ዋና መሠረተ ልማቶች መሆኑን፣ የተቀረው ግን በግሉ ዘርፍ እንደሚገነባ ተናግረዋል፡፡፡

‹‹መንግሥት መንገዶች፣ የባህል ማዕከልና የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎችን ይገነባል፡፡ ሆቴሎች፣ ምግብ ቤቶችና ሌሎች የተለያዩ የቱሪስት አገልግሎት መስጫ ተቋማት መንግሥት ባስቀመጠው ንድፍ መሠረት በግል ባለሀብቶች ይገነባሉ፡፡ መንግሥትና የግሉ ዘርፍ በጋራ የሚያለሙዋቸው ፕሮጀክቶች ይኖራሉ፡፡ አብረው የሚሠሩበት ሞዳሊቲ ይዘጋጃል፡፡ ባለሀብቶች ተወዳድረው በራሳቸው ኢንቨስት የሚያደርጉባቸው ፕሮጀክቶች ይኖራሉ፡፡ ለዚህ የከተማው አስተዳደር ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል፤›› ብለዋል፡፡

አቶ ድሪባ በፕሮጀክቱ ዙሪያ ከዩኒቨርሲቲ ምሁራን፣ ከታሪክ ተመራማሪዎች፣ ከአካባቢ ጥበቃ ባለሙያዎች ጋር ውይይት የሚደረግ በመሆኑ ተቻኩሎ ወደ ግንባታ አይገባም ብለዋል፡፡

ለፕሮጀክቱ የሚያስፈልገው 4.8 ቢሊዮን ብር ከየት እንደሚመጣ የተጠየቁት አቶ ድሪባ፣ በቀጣይ በሚደረጉ ውይይቶች ፕሮጀክቱ ሲዳብር ወጪው ከዚህም ሊበልጥ እንደሚችል ገልጸው፣ አስተዳደሩ ያለው አቅም ውስን እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

‹‹ፕሮጀክቱ በጣም አዋጭ ነው፡፡ ይህን በዓለም ባንክም አስጠንተን አረጋግጠናል፡፡ በመሆኑም ከዓለም ባንክ፣ ከቻይና ኤግዚም ባንክና ከሌሎችም ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት ብድር እናፈላልጋለን፤›› ያሉት አቶ ድሪባ፣ ፕሮጀክቱ በሦስት ደረጃ ተከፍሎ እንደሚካሄድ ገልጸው የንድፍ ሥራው ገና ያልተሠራ በመሆኑ ለመጀመርያው የግንባታ ክፍል ምን ያህል በጀት እንደሚያስፈልግ ሥሌቱ እንዳልተሠራ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ለቱሪዝም ትራንፎርሜሽን ምክር ቤት ባቀረበው የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት የአዲስ አበባ ሙዚየምን በ16 ሚሊዮን ብር ወጪ ማደሱን፣ አራት ኪሎ የሚገኘውን የሚያዝያ 27 የድል ሐውልትና ስድስት ኪሎ የሚገኘውን የካቲት 12 የሰማዕታት መታሰቢያ ሐውልት ቅርስነታቸውን በጠበቀ መልኩ በአምስት ሚሊዮን ብር ወጪ መታደሳቸውን አስታውቋል፡፡ በ2010 ዓ.ም. የዳግማዊ ምኒልክ ሐውልትና በቴዎድሮስ አደባባይ የሚገኘው የሴባስቶፖል ሐውልትን ለማደስ መታቀዱን በሪፖርቱ ተገልጿል፡፡

በዓይነቱ ልዩ የሆነ ባለ 11 ፎቅ የሕፃናትና የወጣቶች ቴአትር ቤት ግንባታ በቅርቡ ተጠናቆ ሥራ እንደሚጀምር፣ የራስ ቴአትር ቤት እንደ አዲስ ለመገንባት በዝግጅት ላይ መሆኑን፣ ደረጃውን የጠበቀ ባለስምንት ፎቅ ዘመናዊ ሲኒማ ቤት ግንባታ በአዲስ አበባ ሲኒማ ቤቶች አስተዳደር ከከተማው አስተዳደር በተገኘ ከ248 ሚሊዮን ብር በላይ የበጀት ድጋፍ ሥራው ተጀምሮ በመፋጠን ላይ መሆኑ ተገልጿል፡፡

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s