ቅዳሜ, ሃምሌ 30
ከጠዋቱ 1:30 አካባቢ ይሆናል መስቀል አደባባይ ስንደርስ። በመንገዶቹ ላይ ወደስራ እና ለተለያየ ጉዳይ የወጡ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ይርመሰመሳሉ።
ከለገሃር ሰማእታት ሃውልት በእግር ነበር የሄድነው። ከሴንጆሴፍ ት/ት ጀምሮ እስከ ሰማእታት ሃውልት ድረስ መሳሪያ ያነገቱ ፌደራሎች በአጭር ርቀት
ልዩነት በተናጠልም ሰብሰብ ብለውም ቆመዋል።
አትኩሮታቸው አላፊ አግዳሚ ላይ ነው። መስቀል
አደባባይ አካባቢ መቆምም መቀመጥም አይቻልም።
ቀይ ማልያ ለብሰው እስፓርት እየሰሩ የነበሩ ወጣቶች
ብቻ ናቸው በዛ ሰአት መስቀል አደባባይን ደፍረውት
የነበረው። ታጥፈን በቦሌ መንገድ ወደፍላሚንጎ
መንገድ ጀመርን፤ የቦሌ መንገድ ተዘግቷል።
ፌደራሎቹ በግራም በቀኝም መሳሪያቸውን ይዘው
ተደርድረዋል፤ ልክ ከውጪ የሚገባ ወይም ከሃገር
የሚወጣ ባለስልጣን ሲኖር እንደሚያደርጉት። ሁለት
ወይም ሶስት ሆነው ታክሲ የሚጠብቁትን ቶሎ ታክሲ
እንዲይዙ ወይም እንዲበተኑ ያስጨንቋቸዋል።
በርከት ብሎ በእግር ማለፍ የማይታሰብ ነው።
ከሁሉም አቅጣጫ ወደ መስቀል የሚያመሩት
መንገዶች በተመሳሳይ መልኩ ተዘግተው ከሆነ ብለን
ወደ ፒያሳ ሄድን። መንገዱ እንደ ቦሌው ባይሆንም
ፌደራሎች ነበሩ። አምባሳደር ጋር ጭራሽ
ከነመኪናቸው ሰፍረዋል። ከፒያሳ ወደ አምባሳደር
ተመልሰን ከዛ በእግር ወደ መስቀል አደባባይ ጉዞ
ጀመርን። ለሰልፉ የተዘጋጁ ወጣቶች በዚህ መልክ
በመታፈናቸው ጉዟችን በብስጭት የታጀበ ነበር።
ግዮን ሆቴልን አለፍ እንዳልን ሰው ግር ብሎ ወደ
መስቀል አደባባይ እየተንጠራራ ያያል። እነሱ ካሉበት
ቦታ ሆነን ምን እንደሚያዩ ለማየት ብንሞክር
አልተሳካልንም። ግልፅ የሆነልን እየተጠጋን ስንመጣ
ነው። መፈክር የያዙ እና የሚያወጡ በርካታ ወጣቶች
መስቀል አደባባይ ላይ ተሰብስበዋል። ከመካከላቸው
ጎልቶ እና ከፍ ብሎ ሚታየውን የ ‘ኦነግ’ ባንዲራ ሳይ
ማመን አልቻልኩም። ከአንድ ሰአት በፊት ያ አደባባይ
እንኳን የ ‘ኦነግ’ ባንዲራ እና መፈክሮችን በያዙ
ቆራጥ ወጣቶች ሊጥለቀለቅ ፤ ሁለት ሰው ቆሞ
ማውራት የሚችልበት አልነበረም። ወዲያውኑ
ጨካኝ፣ አውሬ እና ሰው በላዎቹ ፌደራሎች በአደባባዩ
በሰላማዊ መንገድ ተቃውሟቸውን ያሰሙ የነበሩ
ወጣቶችን በሚዘገንን ሁኔታ ይቀጠቅጧቸው ጀመር።
ከሰው ዘር የተፈጠሩም አይመስሉም። መሃል
አስፓልት ላይ አንድ ወጣት ተደብድቦ ወድቆ ደሙ
መሬት ላይ ይፈሳል። ጭካኔ የተሞላውን ጭፍጨፋ
የተመለከቱ በአካባቢው የነበሩ ሁሉ ጩኸቱን
አቀለጡት። ሲያለቅሱ የነበሩም አሉ። ድብደባውን
አጧጡፈው መንገደኛውንም ወደ አደባባዩ እንሄድ
የነበርነውንም ብቻ ያለ ልዩነት ያገኙትን በቆመጥ
ይከተክቱ ጀመር። እኛ ሮጠን እዛው አካባቢ አንዱ ጋር
ተጠለልን። ይህ ከሆነ ከተወሰነ ደቂቃ በኋላ በርከት
ያለ የተቃውሞ ድምፅ ከመስቀል አደባባዩ አካባቢ
ይሰማን ነበር። እኛ ዱላ ፈርተን ስንሸሽ፤ ዱላው
ያልበገራቸው ወጣቶች ተቃውሟቸውን ሲያሰሙ
ነበር። በድብደባው የተጎዱትን የሚያመላልስ
አምቡላንስ ድምፅ ለረጅም ሰአት ሲሰማ ነበር። ይህ
በእንዲህ እንዳለ ከድብደባ ለማምለጥ በየካፌው እና
ባገኙት ቦታ የገቡትን እየገቡ ሲደበድቡ እና ለቅመው
እየደበደቡ ሲወስዱ እንዲሁም በየመንገዱ እያስቆሙ
መታወቂያ እያዩ ኦሮሞ የሆነ እየመረጡ ሲደበድቡ እና
ሲያስሩ ነው የዋሉት። የወለቁ ጫማዎች እዚህም
እዚያም በየቦታው ተበታትነው ይታዩ ነበር።
ክብር ሞትን ሳይፈሩ መስቀል አደባባይ ላይ ከ11
አመት በኋላ ሰላማዊ የተቃውሞ ሰልፍ ላሳዩን ኦሮሞ
ወጣቶች እና ወዳጆቻቸው!
ክብር ቆራጥነትን እያሳዩን ላሉት ለኦሮሚያ ፣ ጎንደር
እና ባህርዳር [አማራ] ህዝብ!
ክብር መብታቸውን በሰላማዊ መንገድ ሲያቀርቡ
ለታሰሩ፣ ለተደበደቡ እና ለተገደሉ!
#OromoProtests
#AmharaProtests
#EthiopiaProtests